የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ድካምና ወጫችንን ቀንሶልናል - የጎዛምን ወረዳ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሴቶች

107
ባህር ዳር ጥቅምት 7/2011 የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን ለምግብ ማብሰያ መጠቀም በመጀመራችን ድካምና ወጫችንን ቀንሶልናል ሲሉ በምስራቅ ጎጃም ዞን የጎዛምን ወረዳ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሴቶች ገለፁ። በጎዛምን ወረዳ አባ ሊባኖስ ቀበሌ አርሶ አደሮችን በክላስተር አደራጅቶ የባዮ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ያለው በጎ ጅምር በሚመለከታቸው አካላት ተጎብኝቷል። የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ እንዳክመው ወንድም እንደገለፁት ቀደም ሲል ለቤታቸው መጠቀሚያ የሚውል የምግብ ማብሰያ እንጨትም ሆነ ኩበት ለማግኘት ወደ ጫካ በሚያደርጉት ጉዞ እርሳቸውም ሆነ ሴት ልጆቻቸው ለከፋ እንግልት ዳርጓቸው ቆይቷል፡፡ እንዲሁም በጓሯቸው የተተከለውን ባህር ዛፍ በመቁረጥ ለቤት ውስጥ ማገዶ በመጠቀም ከአጠና ሽያጭ ያገኙት የነበረውን ገንዘብም ሲያጡ መቆየታቸውን አመልክተዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በተገነባላቸው የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ሃይል አማራጭ በመጠቀም በቤት ውስጥ እንጀራ መጋገርን ጨምሮ ሌሎች ምግቦችን በማብሰል እንዲሁም የመብራት ሃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም ማገዶ ሲጠቀሙ በሚወጣው ጭስ ይደርስባቸው ከነበረ የጤና እክል ከማስቀረቱም በላይ ያደርሱት የነበረውን የደን ጭፍጨፋ ማቆማቸውን ገልፀዋል። ሴት ልጆቻቸውንም በሰዓቱ ወደ ትምህረት ቤት በመላክ ፊደል እንዲቆጥሩና ተረጋግተው እንዲማሩ እንዳደረጋቸውን አብራርተዋል። በተጨማሪም ከተብላላ በኋላ የሚወጣውን ተረፈ ምርት ለበቆሎ ልማት በማዋል የሰው ሰራሽ ማዳበሪያን ተክተው ማልማት አንዳስቻላቸውም አስታውቀዋል። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዋሌ መልካሙ በበኩላቸው በቅርብ መጠቀም የጀመሩት የሃይል አማራጭ ኩበትና እንጨት ከመልቀም አድኖኛል ሲሉ ተናግረዋል። ምግብ ለማብሰል ረጅም ሰዓት ይወስድ የነበረውን ጊዜ በማሳጠር በአጭር ጊዜ አብስሎ ቤተሰቦቻቸውን በመመገብ ያለአግባብ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ ለሌሎች የግብርና ልማት ስራዎች ለማዋል እንዳገዛቸው ጠቁመዋል። በተለይም ''የመብራት አገልግሎቱ ከኩራዝ ጭስ በማላቀቅ ጨለማውን ገፎልናል'' ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በቀጣይም ለሌሎች ተደራሽ የሆነው የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ አማራጭ የተሰጠው እድል እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል። አርሶ አደሩ በተገነባለት የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ምግብ በማብሰል፣ ለመብራት ሃይልና ተረፈ ምርቱን ለሰብል ልማት እያዋለው ይገኛል ያሉት ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን የውሃ መስኖና ኢነርጅ ልማት መምሪያ የአማራጭ ኢነርጅ ልማት ቡድን መሪ አቶ አምበሉ መሰሉ ናቸው። በዞኑ ከ700 በላይ የባዮ ቴክኖሎጂ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በሦስት የባዮ ቴክኖሎጂ ክላስተሮችን በማቋቋም የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ይገኛል። በተለይም ቀደም ሲል የግብርና፣ የጤናና የውሃና የትምህርት ተቋማት ይስተዋል የነበረውን የቅንጅት ክፍተት በውይይት በመፍታት በጋራ ቴክኖሎጂው ተደራሽ እንዲደረግ እየተሰራ ይገኛል። በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ 370 የባዮ ቴክኖሎጂዎችን መገንባት መቻሉን አስታውሰው በዚህ ዓመት ካምናው ተሞክሮ በመውሰድ 553 ለመገንባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አብራርተዋል። የአርሶ አደሩን አቅም ያገናዘቡ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋትና ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እየተሰሩ ካሉት ስራዎች ከታዳሽ ሃይል የሚገኘው ባዮ ቴክኖሎጂ አንድ ነው ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብረሃም መንገሻ ናቸው። ቴክኖሎጂው ከአርሶ አደሩ የኑሮ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ እስከ 25 ዓመት ማገልገል እንደሚችል የጠቆሙት አቶ አብረሃም የደን ምንጣሮን ለማስቀረትና ''ባዮ ሰላሪው'' /ተረፈ ምርቱ/ ደግሞ ማዳበሪያን በመተካት ምርትና ምርታማነትን በተጓዳኝ ለማሳደግ የሚያግዝ ነው። በክልሉ ከሰባት ሺህ 400 በላይ የባዮ ቴክኖሎጂ ተገንብተው ለአርሶ አደሩ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አመልክተው፤ በዚህ ዓመት ከ3 ሺህ ያላነሱ ግንባታ ለማካሄድ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል። የዚህ የመስክ ጉብኝትም የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ተሞክሮ ማሰየትና አርሶ አደሩ ልምድ እንዲወስድና እውቀት ጨብጦ ቴክኖሎጂውን በራሱ አቅም ግንብቶ እንዲጠቀም ለማነሳሳት እንደሆነም ተናግረዋል። ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጅ ኤጀንሲ የባዮስላሪ ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ከሱ ኩባዮ በበኩላቸው በአማራ ክልል እስከ ታች የሚሰራ የአስራር ስልት መዘርጋቱንና የተሻለ የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ስራ ተፈጥሮ ማየታቸውን ተናግረዋል። ከዚህም በክልላቸው ወስደው ሊተገብሩት የሚያስችል ልምድ መቅሰማቸውን አስታውቀዋል። በጉብኝቱ ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ ባለሙያዎችና ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከደቡብ ክልልና ሌሎች ክልሎችም ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም