በዲላ ከተማ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ይሻሉ፡-ነዋሪዎች

108
ዲላ ጥቅምት 7/2011 በዲላ ከተማ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር በመልካም አስተዳደር ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ከነዋሪዎቹ ጋር አካሂዷል ፡፡ ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት በከተማዋ የሚታዩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሳያገኙ ከዓመት ወደ ዓመት እየተሸጋገሩ ይገኛሉ፡፡ ነዋሪዎቹ በከተማዋ የሚታዩት የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የፍትህ ችግሮች እንደሚታዩና  የመሠረት ልማት ተቋማት፣ለመኖሪያ ቤትና የመሬት አቅርቦት እጥረት እንደሚታይ ገልጸዋል። የፀጥታና የፍትሕ አገልገሎቱም ለኪራይ ሰብሳቢነትና ጠባብ አመለካከት የተጋለጠ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች፣የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ መፍትሄ ሊያበጁላቸው ይገባዋል ብለዋል ፡፡ በከተማዋ የሚስተዋለው የጫትና ሺሻ ቤቶች መበራከትም በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ማግኘት እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል ፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አግዘው ተክለማርያም እንደተናገሩት ዲላ በተራሮችና ወንዞች የተከበበች ለነዋሪዎቿ በቂ ውሃ የማመንጨት አቅም ያላት ከተማ ብትሆንም፤የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሯን ለመፍታት አልቻለችም ፡፡ በዚህም ነዋሪዎቿ በሣምንት አንድ ቀን የመጠጥ  ውሃ  ለማግኘት ተገደዋል ፤ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በወር ለአንድ ቀንም ሳያገኙ ይቀራሉ ብለዋል፡፡ አቶ ከበደ ገብረሃና የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ከገጠር ወደ ከተማው ተካለው መንገድ  ያልተሰራላቸው አካባቢዎች አምቡላንስ ለማስገባት እንኳ  የማይችሉበት ሁኔታ ስለሚታይ መፍትሄ ሊፈግላቸው ይገባል ብለዋል ፡፡ ከፈታ የተደረገላቸው መንገዶችም ቢሆኑ በአግባቡ ያልተቀየሱ መሆናቸውን ያመለከቱት አስተያየት ሰጪ፣በተለይ በከፍተኛ የህዝብ መዋጮ በከተማዋ ውስጥ የተገነቡ የአስፋልት መንገዶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለብልሽት መዳረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡ በከተማዋ ህግ ሲጣስ በቸልተኝነት የሚያልፉ ኪራይ ሰብሰሳቢነት የሚስተዋልባቸው የፀጥታ አካላት እንዳሉም አቶ ከበደ አስረድተዋል ፡፡ የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ትግሉ በቀለ ነዋሪዎቹ ያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች በከተማዋ እንደሚስተዋሉና የችግሮቹን ስፋትና ጥልቀት  ለመረዳትና ከነዋሪዎች ጋር ተባብሮ ለመፍታት ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ፡፡ በከተማዋ በስፋት በየሚስተዋለው የመሠረተ ልማት ተቋማት አለመሟላት ችግር ከገቢ አሰባሰብ ጋር እንደሚያያዝ የገለፁት ከንቲባው፣ ሕገ-ወጥ የንግድ አሠራር  ዋነኛ መንስዔው መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን ብሎም በገቢ ሰብሳቢውም ሆነ በሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለመታገል ከኅብረተሰቡ ጋር  ተቀናጅተው ፈጥረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። የሺሻ ቤቶች መስፋፋት እልባት ለማስገኘት አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጫት ቤቶችን ከትምህርት ተቋማት አካባቢ ለማራቅና የከተማዋን ፅዳትና ውበት ባስጠበቀ መልኩ ህጋዊ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት አቅጣጫ ማስቀመጡንም ከንቲባው አስረድተዋል ፡፡ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ የከተማዋን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የዞኑ አስተዳደር እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ፡፡ የከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር አሳሳቢ ደረጃ የደረሰው ሲደራረቡ በቆዩ ቸግሮች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የከተማው፣ የዞኑ እንዲሁም የደቡብ ክልል አስተዳደርና ሌሎቸ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት 250 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ ነው፡፡ፕሮጀክቱ ከአምስት ዓመታት በላይ ሊፈጅ እንደሚችልም አመልክተዋል። የዞኑ አስተደደር ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ለማበጀት መለሰተኛ የጥልቅ ውሃ ጉድጓዶችን እያስቆፈረ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ በመድረኩ ከከተማዋ ዘጠኙም ቀበሌያት የተውጣጡ ነዋሪዎች፣ የከተማ አስተዳደሩ አካላት እንዲሁም የጌዴኦ ዞን አመራሮች ተገኝተዋል ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም