አምባሳደር አሊ ሱሌይማን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሮማው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር አሊ ሱሌይማን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሮማው ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቀረቡ
52
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 መቀመጫቸውን ፈረንሳይ ያደረጉት በቫቲካን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አሊ ሱሌይማን ለሮማው ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ ፍራንሲስ አንደኛ የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል። አምባሳደር አሊ ከቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ የአገሪቱ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ዋና ፀሀፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ሪቻርድ ጋለገር እና ተወካይ ሚኒስትር ዴኤታ ሊቀ ጳጳስ አንጀሎ ቤኪዩ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል። አምባሳደር አሊ በትምህርቱ ዘርፍ ከአንደኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲኖር የካቶሊክ ቤተክርስትያን ያላትን ሚና አድንቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እና የቫቲካን ሹማምንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት ታሪክ ባለፀጋ ከመሆኗ በተጨማሪ በቫቲካን ክልል ከአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የራሷ ገዳም ያላት፣ ከ1919 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ ኮሌጅ ባለቤት በመሆን ረጅም ታሪክ ያላት መሆኗን አውስተዋል። በአሁኑ ወቅት ቤተክርስሷያኗ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ባላት ተሰሚነት እና ብዙ ሀይማኖቶች በመቻቻል የሚኖሩባት አገር በመሆኗ ልዩ ትኩረት የሚሰጣት አገር እንደሆነች መግለጻቸውን መግለጫው አትቷል።