ተቋማት በአዲስ መልክ መደራጀታቸው የሀገር ሀብትን ለዘላቂ ልማት የመጠቀም አቅምን ያሳድጋል… የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

67
ጥቅምት 7/2011 ተበታትነው ሲሰሩ የነበሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ባለቸው የስራ ተቀራራቢነት በአንድ ተቋም ስራ መደራጀታቸው የሀገርን ሀብትን በመቆጠብ ለዘላቂ ልማት ለማዋል እንሚያስችል አስተያየታቸውን የሰጡ  የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ሴቶችን በከፍተኛ ውሳኔ ሰጪነት እኩል ተሳታፊ ማድረጉ በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሴቶችን ያማካሉ ለማድርግ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የተገለጹት። በአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ  የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አበባ ተሰማ  በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት በአንድ ተቋም መሰራት የሚችሉ ስራዎችን በሁለትና ሶስት ተቋም በመከፋፋል እርስ በርስ ስራን የመነጣጠቅ ሁኔታ እንደነበር ነው ትዝብታቸውን የገለፁት። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለቤት ኪራይና ለስራ ማስኬጃ የሚያወጡት ከፍተኛ በጀት ለልማት በሚውል በጀት ላይ ጫና ያሳድራል ያሉት አቶ አበባ ተቋማቱ በአዲስ መልክ መደራጀታቸው የሀገርን ሀብት በቁጠባ በመጠቀምና ለድህንት ቅነሳ ፕሮግራሞች ማዋል እንደሚያስችል  ነው የገለጹት፡፡ መንግስት ሴቶችን በከፍተኛ አመራርነት ላይ እኩል ተሳታፊ ማድረጉ በሁሉም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውሳኔዎች የሴቶች ተጠቃሚነትን ያማከሉ እንዲሆኑ ያደርጋል ያሉት ደግሞ  በንግድ ስራ  የተሰማሩት  ወይዘሮ ሀይማኖት ሀይለመስቀል ናቸው፡፡ ሴቶች ለሰላም መጠበቅ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በሀገሪቱ ከፍተኛ አመራርነት እኩል መሳተፋቸው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በማምጣት በኩልም በጎ አስተዋጽኦ እደሚኖራቸው  ነው  የጠቆሙት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ከፍተኛ የአመራርነት ቦታዎች የሴቶችን ተሳትፎ ከወንዶች እኩል ማድረጋቸው በሀገሪቱ አዲስ ታሪክ መሆኑንና ሴቶች ይበልጥ ጠንክረው እንዲሰሩ  የሚያበረታታም  ነው ብለዋል፡፡ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሪፎርሙ 28 የነበሩትን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች  ወደ 20 በመቀነስ፤ የሴት ሚኒስትሮችን ተሳትፎ 50 በመቶ በማድረግ በትላንትናው እለት  የቀረበለትን እጩዎች ተቀብሎ አጽድቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም