ኢትዮጵያ ብሔራዊ የህጻናት ጉዳይ ፖሊሲ ልታዘጋጅ ይገባል-የአፍሪካ የህጻናት መብትና ደህንነት ባለሙያዎች ኮሚቴ

120
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 የአፍሪካ የህጻናት መብትና ደህንነት ባለሙያዎች ኮሚቴ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የህጻናት ጉዳይ ፖሊሲ እንድታዘጋጅ ምክረ ሀሳብ አቀረበ። ኮሚቴው በኢትዮጵያ ያለውን የህጻናት መብትና ደህንነት ይዞታን በሚመለከት አደረኩት ባለው ምልከታ ለህጻናት መብት ሲባል በየተቋማቱ በጀት የመመደብ ጅምር ስራ መከናወኑን አረጋግጫለሁ ብሏል። የባለሙያዎች ኮሚቴውን ጥናታዊ ጽሁፍ ለባለድርሻ አካላት ያቀረቡት አቨር ጋቫር እንደገለጹት ህጻናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ለማድረግና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የህጻናት ማዕከላት የመሳሰሉ አደረጃጀቶች መፈጠራቸውንም አድንቀዋል። ይሁንና በጉዳዩ ላይ የተሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት አጽንኦት ሰጥቶ ቢሰራቸው ብሎ ኮሚቴው ያዘጋጃቸውን ምክረ ሀሳቦች ለባለድርሻ አካላት በዝርዝር አቅርበዋል። የህጻናትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረግ ህገወጥ ጉዞንና እድሜያቸው ሳይደርስ ትዳር እንዲመሰርቱ የሚደረጉ ህጻናትን ጉዳይ በሚመለከትም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቋል። በሴተኛ አዳሪነት ላይ የተሰማሩ ህጻናት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚገኙም ሀገሪቱ ይህን የሚከለክለውን ዓለም አቀፍ ህግ ተቀብላ እንድትተገብረውም ምክረ ሃሳብ ቀርቧል። በጤና ተቋማት ህጻናት በበቂ ሁኔታ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግና በትምህርት ቤቶችም መምህራን ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንዲያስተምሩ በማድረግ በኩል ክፍተት በመኖሩ ለሁሉም ችግሮች መንግስት ብሔራዊ የህጻናት ጉዳይ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ሊተገብረው እንደሚገባም ኮሚቴው መክሯል። የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኦሞት በበኩላቸው ከአፍሪካ የህጻናት መብትና ደህንነት ባለሙያዎች ኮሚቴ የቀረቡትን ምክረ ሀሳቦች የመተግበር እንቅስቃሴ ቀደም ብሎ መጀመሩን ለኢዜአ ተናግረዋል። በተለይም የህጻናት ህገወጥ ዝውውር በሚታይባቸው አማራ ደቡብና ትግራይ ክልሎች ላይ ማዕከላትን በማቋቋም ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ኮሚቴው ባቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት የህጻናትን ልደት በ90 ቀናት ውስጥ በመመዝገብ የትምርትና የጤና አገልግሎት ጥቅሞቻቸውን ለማረጋገጥም ይሰራል ብለዋል። አጠቃላይ የህጻናት ጉልበትና ወሲብ ብዝበዛን ለማስቆምም በኮሚቴው የቀረበውን ምክረ ሃሳብ ለመተግበር ሚኒስቴሩ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም