ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 50 በመቶ ሚኒስትሮችን ሴቶች ማድረጓ በአፍሪካ ሆነ በዓለም በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው…አለማቀፍ ሚዲያዎች

82
ጥቅምት 7/2011 ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 50 በመቶ የሚኒስትር አባላትን ሴቶች ማድረጓ በአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስና በዓለም ከፍተኛ የሴቶችን ቁጥር ካካተቱ ስድስት ሀገራት  ውስጥ አንዷ መሆኗና  ውሳኔውም አስደናቂ  መሆኑን አለማቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ቢቢሲ፣ አልጄዚራ፣ ዘ-ጋርዲያን፣ ሮይተርስ፣ አናዶሉ ኤጀንሲ፣ ኤስቢኤስ፣ ዘ-ኢንዲፐንደንት፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ዴይሊ ሜይል እና ሌሎችም ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በትናንትናው እለት ለህዝብ  ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ስላፀደቁት ካቢኔ  ዘገባዎችን ሰርተዋል፡፡ የአፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ  በትናንትናው እለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ስላፀደቁት  ሚኒስትሮች  ባሰፈሩት  ዘገባ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 50 በመቶ  ሴቶች ሚኒስትሮችን መሾሟ በአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስና በዓለም 6 ከፍተኛ ቁጥር የሴት ሚኒስተሮች ካሏቸው ሀገራት  አንዷ  እንደሆነች እና ውሳኔውም አስደናቂ ነው ብለዋል ፡፡ ይህ ሴት ሚኒስትሮችን በእኩልነት መሾም ሴቶች መምራት አይችሉም የሚለውን የቆየና ኋላቀር አስተሳሰብን የሚቀይር ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ ሚዲያዎቹ በዘገባቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቁልፍ የፀጥታና ደህንነት ቦታዎች ለሴቶች መሰጠታቸውን  የጠቀሱ ሲሆን  ለዚህም  ለሰላም ሚኒስትርነት ወይዘሮ ሙፈሪያ ካሚል  እንዲሁም ለመከላከያ ሚኒስትርነት ኢንጅነር አይሻ መሀመድ መሾማቸው ትልቅና አስገራሚ ውሳኔ  እንደሆነ  በዘገባቸው አስፍረውታል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር የተቋቋመበት ዋና ምክንያትም የተጀመሩት የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲሰፉና እንዲቀላጠፉ ለማስቻል መሆኑንም  ዘግበዋል፡፡ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት፣ የሀብት ብክነትን ለመከላከልና ሀብትን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ የመንግስት ተቋማትን በአዲስ መልክ ማደራጀቱንና የካቢኔ አባላት ቁጥርም ወደ 20 ዝቅ እንዲል መወሰኑን አንስተዋል። አዲሱ ካቢኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመሩትን ሁለገብ የማሻሻያ ስራ ለማፋጠን ያለመ ነው መባሉን በሚዲያዎቹ ዘገባ ሽፋን የተሰጠው ነው ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ እየወሰዷቸው ያሉት በሳል እርምጃዎችም ከኔልሰን ማንዴላ፣ከባራክ ኦባማ፣ ከጀስቲን ትሩዶና ከሌሎች የለውጥ መሪዎች ጋር እንደሚያመሳስሏቸውም በአለማቀፍ ሚዲዎቹ ተጠቅሷል፡፡ መረጃውን ያደረሰን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ነው  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም