በኢትዮጵያ 70 ሺህ ሴት ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነገ ይፋ ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ 70 ሺህ ሴት ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነገ ይፋ ይሆናል
70
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 የእንግሊዝ ኤምባሲ በኢትዮጵያ 70 ሺህ ሴት ተማሪዎችን በመደገፍ ውጤታማ የሚያደርገውን ፕሮጀክት ነገ በአዲስ አበባ ይፋ ያደርጋል። ኤምባሲው ፕሮጀክቱን በማስመልከት ዛሬ በአጼ ቴዎድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማብሰሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል። የእንግሊዝ መንግስት በርካታ አገራት በተለያየ መንገድ ሴቶችን በትምህርት ለመደገፍ ለሚያደርጉት ጥረት እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል። "አንድም ሴት ወደኋላ መቅረት የለባትም" የሚል ዘመቻ በማካሄድም በ150 አገራት የሴት ተማሪዎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ ነው። በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር አሌክስ ካሜሮን እንዳሉት ዓለም አቀፍ ዘመቻው ሴቶች ጎጂ በሆኑ ማህበራዊና የኑሮ ሁኔታ ሳቢያ በአግባቡ ከመማር እንዳይስተጓጎሉ መከላከልን መሰረት ያደረገ ነው። መንግስታቸው በኢትዮጵያም ባለፉት 12 ዓመታት ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል። ያልተማሩ ሴቶችን ቁጥር በመቀነስ ህይወታቸው እንዲሻሻል በማድረግ በሙሉ አቅም መስራት እንዲችሉ እገዛ ማድረጉንም እንዲሁ። "ሴቶችን ማስተማር አገርን ማበልጸግ ነው" ያሉት ምክትል አምባሳደሩ ሴቶች ከተማሩ የራሳቸውን መጻኢ ዕድል ማስተካከልና ማህበረሰባዊ ለውጥ በማምጣት አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ሴቶች ጤናቸው ተጠብቆ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ፣ በራስ መተማመናቸው እንዲጎለብት እንዲሁም ያለዕድሜ ጋብቻ በመውለድና በቤት ውስጥ ስራ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ መስራት የመርሀ ግብሩ አካል እንደሆነም ጠቁመዋል። ቤተሰብና ማህበረሰቡን ሴቶችን ማስተማር ስለሚኖረው ጠቀሜታ ማስገንዘብ፣ ሴቶች ስለ ህይወትና ስራ መሰረታዊ ክህሎት እንዲጨብጡ ማድረግም የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አብራርተዋል። በእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ 70 ሺህ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የትምህርት ክትትልና ቆይታቸውን የሚያቃልል አገር አቀፍ ፕሮጀክት ነገ ይፋ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።