በሲዳማ ዞን በአገዳ ሰብሎች ላይ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል….አቶ ደሴ ዳልኬ

3981

ሀዋሳ ግንቦት 13/2010 በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በአገዳ ሰብሎች ላይ የተከሰተውን አሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ በበልግ እርሻ በአገዳ ሰብሎች በተሸፈነ ማሳ ላይ የተከሰተውን ተምች ለመካላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ዛሬ በዞኑ ቦረቻ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

አቶ ደሴ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የተለያዩ የአርሶ አደር አደረጃጀቶችን በመጠቀም ተምቹን ለመከላከል እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

አርሶ አደሩ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ክስተት የቀሰመውን ተሞክሮና የባለሙያን ምክር ተቀብሎ እያከናወነ ባለው ተግባር እስካሁን ጉዳት አለመድረሱን በጉብኝቱ ወቅት መታዘባቸውንም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በአገዳ ሰብሎች መሸፈኑን ተናግረዋል።

በበልግ እርሻ ከለማው ከእዚህ ማሳ ውስጥ አሜሪካ መጤ ተምች በ12 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ መከሰቱን ገልጸው፣ በለቀማና በኬሚካል ርጭት ተምቹን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ተምቹ ጉዳት በሰብል ላይ እንዳያደርስ ለማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል

በተለያዩ ቀበሌዎች በተደረገው ጉብኝት የዞኑ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡