ዩኒቨርሲቲው ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን አስታወቀ

52
ዓርባ ምንጭ ጥቅምት 7/2011 የዓርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንቱ  ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ  ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ተወያይቷል። የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ትናንትበዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ነባርና አዲስ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች  ያሰለጥናል። ከነዚህም ከ6ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አዲስ እንደሚሆኑም ገልጸዋል። ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገቡ በማህበራዊ ህይወታቸው ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የክህሎት ትምህርት እንደሚሰጥም አመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከጥቅምት 11 እና 13 የነባር ተማሪዎች ቅበላ የሚያከናውን ሲሆን፣ ጥቅምት 15ና 16/2011 ደግሞ አዲስ ገቢዎችን እንደሚቀበል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል። ተማሪዎቹ ከአቀባበል ጀምሮ በመማር ማስተማር ሂደት ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያስረዱት ዶክተር ዳምጠው፣ ከግቢ ውጭ ችግር እንዳያጋጥማቸው የከተማው ነዋሪዎች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ዩኒቨርሲቲው ከፖለቲካ፣ ኃይማኖትና ከትምሀርት ጋር  ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች የጸዳ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የዓርባ ምንጭ ከተማ የሰላም ፎረም አባል አቶ ገረሱ በየነ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ተግባሩን ለማከናወን እንዲያስችለው የሰላም ፎረም እንዲያቋቁም አሳስበዋል። ሌላኛው የኃይማኖት አባት መጋቢ ካሳዬ በየነ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ እየተስፋፉ የመጡትን የሺሻ፣ የጫትና የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል። የዓርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከውሃና ከኤሌክትሪክ መቆራረጥ ጋር የሚያጋጥሙትን ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚታዩ ህገ ወጥ የሺሻ፣ የመጠጥና ጭፈራ ቤቶችን በመቆጣጠርና በመከታተል እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። በውይይቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የከተማው የሰላም ኮሚቴ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም