የህክምና መሳሪያዎች በአገር ውስጥ ሊመረቱ ነው

84
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 ከውጭ የሚገቡ የህክምና መሳሪያዎች በአገር ውስጥ ሊመረቱ ነው። ኢትዮጵያ በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከውጭ ለሚገቡ የህክምና መሳሪያዎች እንደምታወጣ መረጃዎች ያሳያሉ። የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው በ2010 በጀት ዓመት ብቻ ለህክምና መሳሪያ ግዥ 153 ሚሊዮን ዶላር ወጥቷል። ከዚህ ውስጥ ሶስት ሚሊዮን ደላር የህሙማን አልጋ፣ የጉሉኮስ መስቀያና ሌሎች በአገር ውስጥ ሊመረቱ ለሚችሉ መሳሪያዎች ግዥ የወጣ ነው። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ተስፋለም አድራኖ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የህክምና መሳሪያዎችን ከውጭ ታስገባለች። ለነዚህ መሳሪያዎች ከዓመት ዓመት የተለያየ ቢሆንም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ ግዥ እንደሚፈጸም ነው የሚናገሩት። ውስብስብና በዓለም በተወሰኑ አምራቾች ብቻ የሚመረቱ እንዲሁም በቀላሉ በአገር ውሰጥ ሊመረቱ የሚችሉንት ጨምሮ የሚወጣው የውጭ ምንዛሬ አሳሳቢ መሆኑን ነው የሚናገሩት። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት በአገር ውስጥ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ መሳሪያዎችን ለማምረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል። ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሹመቴ ግዛው እንደተናገሩት ኢትዮጵያን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስከፈሏት ካሉ ዘርፎች አንዱ የጤናው ዘርፍ ቀዳሚ መሆኑን በመለየት መርፌ፣ ጓንት፣ የህሙማን አልጋን ጨምሮ ሌሎች በአገር ውስጥ በቀላሉ ሊመረቱ ከሚችሉ መሳሪያዎች ለመጀመር ታስቧል። በቀጣይ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥም አጠቃላይ የእቅድ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ነው ያረጋገጡት። ምርቱን ለማስጀመር አገር ውስጥ ያሉ የግልና የመንግስት ፋብሪካዎች የትኞቹን ማምረት ይችላሉ? የሚለውም እየተለየ ነው ተብሏል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጉ ያሉ ምርቶችን በመለየት የሳይንስ ፈጠራዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር እየሰራሁ ነው ብሏል። ኢትዮጵያ ከህሙማን አልጋዎች ጀምሮ ሲቲ ስካን፣ ኤም.አር.አይ፣ የካንሰር ህክምና መሳሪያዎችና ሌሎች ትላልቅ መሳሪያዎችን ከውጭ ከምታስገባቸው መሳሪያዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም