አዲስ የሚሾሙት አፈጉባኤ ቋሚ ኮሚቴዎችን ማጠናከር ላይ ትኩረት መስጠት አለባቸው-ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

85
አዲስ አበባ  ጥቅምት 6/2011 አዲስ የሚሾሙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቋሚ ኮሚቴዎችን ማጠናከር ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ተሰናባቿ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ውይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጥሪ አቀረቡ። ወይዘሮ ሙፈሪያት አዲስ ለተቋቋመው የሰላም ሚኒስትር ውጤታማነት ሁሉም ዜጋ ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ምክር ቤቱን ለስድስት ወራት ያህል በአፈ ጉባኤነት ሲያገለግሉ የነበሩትን ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የመልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሎ አዲስ ለተቋቋመው "የሰላም ሚኒስቴር" ሚኒስትር አድርጎ ሾሟቸዋል። ሚኒስትሯ ከሹመቱ በኋላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ጥቂት ወራቶች የምክር ቤቱን ቋሚ ኮሚቴ ማጠናከርን ያለሙ ጥናቶች ተካሄደዋል። ቋሚ ኮሚቴዎች በአሰራር በተልዕኮና በአደረጃጀት መጠናከር እንዳለባቸው ጥናቶቹ ማመላከታቸውን ጠቁመው፤ እርሳቸውን የሚተኩት አፈ ጉባኤ ይህን ተልዕኮ እንደሚያሳኩ ያላቸውን አምነት ገልጸዋል። የዴሞክራሲ ዋና መገለጫ የሆነው የህግ የበላይነትና ፍትሃዊ አሰራር እንዲሰፍን ከምክር ቤቱ በተጨማሪ እያንዳንዱ ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት የሰላም መጥፋት የኢትዮጵያውያን መገለጫ አለመሆኑን ተናግረው፤ "እያንዳንዳችን መገለጫችን የሆነውንና  የእርቅና የመከባባር እሴቶቻችንን መጠበቅ አለብን" ብለዋል። አዲስ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ዜጎች በእጃቸው ያለውን የሰላም እሴት እንዲያስተውሉት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል። የአገርን ሰላም ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ  ጉዳይ መሆኑን አምነው ወደ ሃላፊነት እንደመጡ የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ ህዝብ ይህን በመረዳት ከጎናቸው ሆኖ እንደሚያግዛቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት በተለያየ የመንግስት ስራ ኃላፊነት ላይ ተመድበው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ የለውጥ ሰው መሆናቸውን ዛሬ ለሰላም ሚኒስትርነት ዕጩ አድርገው ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ገልጸዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሊቀመንበር ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም