የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘመናዊ የመረጃና ግንኙነት ስርዓት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

67
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዜጎች ጋር ሊኖረው የሚገባውን ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላል ያለውን ዘመናዊ የመረጃና ግንኙነት ስርዓት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ። ስርዓቱ ግልፅ የሆነ የምክር ቤት አሰራርን በማስረጽ ዜጎችን ከምክር ቤቱ፤ ምክር ቤቱን ደግሞ ከዜጎች ጋር በቀላልና በተቀላጠፈ መንገድ የሚያገናኝ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ ስርዓት ነው ተብሏል። ምክር ቤቱ ላለፉት ሶስት ወራት ሲያከናውን የነበረውን ይህንኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የመረጃና ግንኙነት የአሰራር ስርዓት ፕሮጀክት ትላንት ምሽት አስመርቋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዜጎች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የቀድሞ አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት ተናግረዋል። ወይዘሮ ሙፈሪያት እንዳሉት የመረጃ አያያዝን ዘመናዊ ማድረግ፣ በጥናትና ምርምር የታገዙ ስራዎችን መተግበር በፕሮጀክቱ ከተከናወኑት ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ። የመረጃ ስርዓቱ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚያከናውኗቸውን የክትትልና የድጋፍ ስራዎች ለማቀላጠፍ፣ ህብረተሰቡ ስለመንግስት ተቋማት አሰራር  ማወቅ የሚገባውን መረጃ በቀላሉ የሚያገኝበትን ሁኔታ ጨምሮ አጠቃላይ የምክር ቤቱን አሰራር ግልፅነትና ፍጥነት የሚያጠናክር ነው ተብሏል። ጥራት ያለው የክትትልና የድጋፍ ስራን ከመስራት ባሻገር የተቋማትን አፈጻጸም ፍትሃዊ ለማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው ወይዘሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል። ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው  የፌዴራልና የክልል መንግስታት የሚመለከተውን በመለየት ሃሳብና አስተያየት የሚሰጥበት አሰራርም እንዲሁ። በአሁኑ ወቅት ምክር ቤቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ከህዝቡ ጋር በሚያደርገው ውይይት የህዝብ ውክልና ስራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ለማለት እንደሚያዳግት ወይዘሮ ሙፈሪሃት ገልፀዋል። በመሆኑም ዘመናዊው የመረጃና መገናኛ ስርዓቱ ህዝቡን በሚፈለገው ጊዜና መጠን ለመቅረብ እድል ከማስፋት ባሻገር መንግስትና ህዝብንም ለማቀራረብ ከፍተኛ ሚና የጫወታል ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም