የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ሊመሰረት ነው

88
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2010 የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፈደሬሽን ከሁለት ቀን በኋላ እንደሚመሰርት የኮንፌደሬሽኑ አደራጅ ምክር ቤት አስታወቀ። የምክር ቤቱ ሰብሳቢና የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ አሰሪዎች ፌደሬሽን ሰብሳቢው አቶ ጌታቸው ኃይሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት በተለያዩ ዘርፎች የተቋቋሙ አምስት አሰሪ ፌደሬሽኖች የጋራ ኮሚቴ አዋቅረው አንድ ኮንፌደሬሽን ሊመሰርቱ ነው። የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጭ አሰሪዎች፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አሰሪዎች፣ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሰሪዎች፣ የአማራ ክልል አሰሪዎች እና የአዲስ አበባ ከተማ አሰሪዎች ፌደሬሽኖች መስራች አባላት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ፌደሬሽኖቹ በአዲስ አበባ የ'አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን መስራች ጠቅላላ ጉባኤ' በማካሄድ ኮንፈደሬሽኑን በይፋ እንደሚመሰርቱም ነው የገለጹት። በኢትዮጵያ ስድስት የአሰሪዎች ፌደሬሽኖች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤  ኮንፌደሬሽን ለመመስረት በነበረው ሂደት 'ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን በስተቀር ቀሪዎቹ አንድ ኮንፌደሬሽን ለመመስረት ተስማምተው መወሰናቸውን አብራርተዋል። ማህበራቱ ወደ ፌደሬሽን ከማደጋቸው በፊት 'የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን' ሲያስተባብር መቆየቱን ገልጸው፤ በፌደሬሽን ደረጃ ከተዋቀሩ ወዲህ ግን ራሳቸውን ችለው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ተናግረዋል። የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ አሰሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፍትሕ ወልደሰንበት በበኩላቸው የኮንፌደሬሽኑ መመስረት በተመሳሳይ የአደረጃጀት ደረጃ ለመወያያትና ከሰራተኛ ጋር የሚኖረውን የኢንዱስትሪ ሰላም ለማስፈን ያለመ መሆኑን አመልክተዋል። በወቅቱ ያለው አደረጃጀት ሁሉንም ወገን ያካተተና የሁሉን ድምጽ ይዞ የሚንቀሳቀስ እንዳልነበር ገልጸው፤ የአሰሪዎች ፌደሬሽኖችን የመደራደር አቅም ለማጎልበት፣ መብታቸውን ለማስከበርና ግዴታቸውንም በዕውቀት ላይ ተመስርተው ለመወጣት ያግዛል ብለዋል። ከነገ በስትያ በሚደረገው የኮንፌዴሬሽን ምስረታ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሲቪክ ማህበራትና የአገሪቱ አሰሪዎች እንደሚገኙ አደራጅ ምክር ቤቱ አረጋግጧል። በሌላ በኩል በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚመሰረተው ኮንፌደሬሽን ራሱን ያገለለው 'የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን' ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ.ም የአባል ማህበራት ጉባኤ መጥራቱ ታውቋል። በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት ኮንፌደሬሽን የሁሉም ፌደሬሽኖች ጥላ ሆኖ አሰሪው ከመንግስትና ሰራተኛው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለማሳለጥ የሚቋቋም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም