ለዶክተር አብይ አህመድና ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ጥረት የጋሞ አገር ሽማግሌዎች እውቅና ሰጡ

118
አርባ ምንጭ  ጥቅምት 5/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ አገራት መካከል ተፈጥሮ የቆየውን ቅራኔ በሰላም እንዲፈታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የጋሞ አገር ሽማግሌዎች እውቅና ሰጡ ። የጋሞ ባይራ ሽማግሌዎች የሁለቱ ሀገር መሪዎች ለፈጸሙት ገድል "ጋሻና ጻንባሮ" የተባሉ ውድ የብሔረሰቡ ባህላዊ እርቀ ሰላም ማስፈጸሚያ መሳሪያዎችን በሽልማት አበርክተዋል። መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ የተቀሰቀሰው ጸብ እንዲበርድ የአገር ሽማግሌዎቹ በሳር ላከናወኑት ባህላዊ እርቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላበረከቱላቸው ስጦታም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሽማግሌዎቹ ሳር በማጨድ ሁለቱ መሪዎች "ቀሪ የሥራ ዘመናቸው ይለምልም " ብለው የመረቁ ሲሆን እስካሁን ለአገርና ለቀጠናዊ ሰላም ላበረከቱት አስተዋጽኦም ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል። በፕሮግራሙ የታደሙ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምናና የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎችም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአገር አንድነትና ለሃይማኖቶች መቻቻል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸው አቅርበዋል። "ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ ሆነው የጀመሩትን አገራዊ የለውጥ ጉዞ አጠናክረው እንዲቀጥሉ " ሲሉም ገልጸዋል። የደቡብ ክልል ርዕሰ መስትዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ባለፋት ስድስት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር የተገኙ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በክልሉ ከዴሞክራሲ ጉድለት ከህዝቡ እየተኑ ያሉ ቅሬታዎችን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ለተሰጣቸው ስጦታ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በበኩላቸው የአገር ሽማግሌ አስታራቂ፣ አስተዋይና ጥበበኛ መሆን እንዳለበት ገልጸው "ሌሎችም ከእነሱ እንዲማሩ እንሠራለን" ብለዋል። የጋሞ ባይራዎች በመስከረም 11ዱ የአርባ ምንጭ ግጭት የወጣቶችን ቁጣ ለማብረድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሠለም ተምሳሌት የሆነች የርግብ ምስል ስጦታ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማበርከታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም