የሱልጣን ዓሊሚራህ ሐንፍሬና የልጅ ኢያሱ ቤተ-መንግሥታት ጥገና እያደረገ መሆኑን ቢሮው ገለጸ

49
ሰመራ ጥቅምት 5/2011 የሱልጣን ዓሊሚራህ ሐንፍሬና የልጅ ኢያሱ ቤተ-መንግሥታት ጥገና እያደረገ መሆኑን የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። በቢሮው የባህል ሃብትና ቅርስ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ሐቢብ መሐመድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  እንዳስረዱት ቢሮው በዚህ ዓመት የቤተ መንግሥታቱን ጥገና ከቅርስ ጥናትና ጥበቃና ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር መድቦ በማደስ ላይ ነው። ክልሉ ያሉትን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በመጠበቅና በመንከባከብ ለቱሪስት መስህብነት ለማዋልም ለረጅም ዘመናት እንክበካቤና ጥበቃ ባለማግኘታቸው በመፈራረስ ላይ የነበሩትንና የአዉሳ ሱልጣኔት መናገሻ በነበረችው አይሳኢታ ከተማ የሚገኙት ቤተ መንግሥታት እድሳት መጀመሩን ተናግረዋል። በዚህም ከ1944 ጀምሮ የአዉሳ ሱልጣኔት መሪ የነበሩት የሱልጣን ዓሊሚራህ ሐንፍሬና ከ1913-16 የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት የልጅ ኢያሱ ቤተ መንግሥታት እድሳት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ልጅ ኢያሱ መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገባቸዉ በኋላ በግዞት የኖሩበት ከአይሳኢታ ከተማ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው ቤተ-መንግሥት እድሳት እስከዚህ ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በአይሳኢታ ከተማ የሚገኘው ባለ ሦስት ፎቅ የሱልጣን ዓሊሚራህ ሐንፍሬ ቤተ መንግሥት እድሳት በቅርቡ እንደሚጀምርም ገልጸዋል። በቀጣይም በአርጎባራና ሰሙሮቢ- ገለአሎ ወረዳዎች የሚገኙ እስከ 500 ዓመታት የሚገመት ዕድሜ ያላቸው ጥንታዊ መስጂዶችን ለማደስ ጥናቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አቶ ሐቢብ አመልክተዋል። የአይሳኢታ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጀማል አህመድ በሰጡት አስተያየት የሱልጣን ዓሊሚራህ ሐንፍሬ ቤተ መንግሥት በከተማዋ መሃል ላይ የሚገኝ ዘመናዊና ለከተማዋም ውበት ሆኖ የቆየ ሕንፃ እንደነበር አስታውሰው፣የሕንፃውን ታሪካዊነቱን ከግምት በማስገባት የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የተጀመረው እድሳት የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማጠናከር አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። በዕደ-ጥበብ ውጤቶች ሽያጭ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ አይሻ ቤተ መንግሥታቱን ታድሶ ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል የተጀመሩት ሥራዎች በወረዳው የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችንና  የጎብኚዎችን ቁጥር እንደሚያሳድጉ እምነታቸውን ገልጸዋል።በሥራቸው ከጎብኚዎች የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል። ክልሉ የሱልጣን ዓሊሚራህ ሐንፍሬ ቤተ-መንግሥትን ጨምሮ የበርካታ እስላማዊ ቅርሶች መገኛና  ከታሪካዊ ፋይዳው ባለፈ፤ የኅብረተሰቡን ባህልና ሥልጣኔ ገላጭ ቅርሶችን በመንከባከብና በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም