በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ህግና ስርዓትን ተመርኩዘው መቅረብ አለባቸው-የምክር ቤቱ አባላት

65
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2011 በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ህግና ስርዓትን ተመርኩዘው መቅረብ እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አመለከቱ። 11ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ምክንያት በማድረግ የምክር ቤቱ አባላት ዛሬ ውይይት አካሂደዋል። አባላቱ በውውይቱ ላይ እንዳነሱት፤ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ላይ ህገ ወጥ ተግባራት እየተስተዋለ ነው። የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን መሆን እንዳለበትና በቀጣይ በቂ ግንዛቤ መሰራት እንዳለበት የሚገልጹ ሃሳቦች ተነስተዋል። የምክር ቤቱ አባል አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ግዜ እንዳሉት፤ በተለያየ ጊዜ ህገ መንግስቱ ከሚደነግገው ሰንደቅ ዓላማ ውጭ የሆኑ ሌሎች ሰንደቅ ዓላማዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ እየተስተዋለ ነው። አሁን የሚታዩ ችግሮች ሰንደቅ ዓላማው ለአገር ያለውን ትርጉም፣ ከመንግስት መዋቅርና ሌሎች ነገሮች ጋር የሚያያዝ አለመሆኑን ጠቁመዋል። ''በሰንደቅ ዓላማው በተቀመጠው ላይ በቂ መግባባት አልተፈጠረም'' ያሉት አምባሳደሩ ሰንደቅ ዓላማውን ከስርዓትና ግለሰቦች ጋር የማያያዝ ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል። ይህም የሚያሳየው ህገ-መንግስቱ ላይ ከመጽደቁ ውጪ በትውልዱ ዘንድ በቂ ግንዛቤ እንዳልተፈጠረ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል። ''በአገሪቷ የተጀመረው ዴሞክራሲን የማስፋት ስራ የህግ የበላይነት ከማስከበር ጋር አብሮ ካልሄደ ከባድ ነው'' ያሉት እንደራሴው ማንኛውም ወገን ሀሳቡን ሲያቀርብ በህጋዊ መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል። የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመረው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበት ተግባራት መከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል። ''መገናኛ ብዙሃንም በሰንደቅ ዓላማው ዙሪያ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን ሀሳብ በእኩል ማስተናገድ ይኖርበታል፤ ምክር ቤቱም ጉዳዩ ወደ ተግባር እንዲቀየር የበኩሉን ሚና ይወጣል'' ሲሉ ተናግረዋል። የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም በበኩላቸው ወቅቱ በሀሳብ የበላይነት አሸንፎ የሚወጣበት ጊዜ እንደሆነ አመልክተዋል። በሰንደቅ ዓላማው ዙሪያ ዝርዝር ነባራዊ ሁኔታውን የሚተነትን ጥናት መካሄድ እንዳለበት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ''የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያምንበትን አቋም ይዞ ይሂድ'' ሲሉም ተደምጠዋል። ''ለውጡን በሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ላይ ተመስርተን መደገፍ የሁላችነም ኃላፊነት ነው'' ብለዋል። ሰንደቅ ዓላማው የአንድነት መገለጫ መሆኑን የተናገሩት አቶ አማኑኤል በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያሉ ልዩነቶች መቅረብ ያለባቸው ህግና ስርዓትን ጠብቀው እንደሆነ ገልጸዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም