ሰንደቅ ዓላማን አስመልክቶ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በቂ መድረኮች አልተፈጠሩም-አፈ ጉባዔ አበበች ነጋሽ

74
አዲስ አበባ  ጥቅምት 5/2011 ሰንደቅ ዓላማን አስመልክቶ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በቂ መድረኮች እንዳልተፈጠሩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  ወይዘሮ አበበች ነጋሽ  ተናገሩ። ምክር ቤቱ 11ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አስመልክቶ ዛሬ አባት አርበኞችና የከተማው ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ ሰርዓት አካሄዷል። አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአገሪቱ በስራ ላይ ያለውን ሰንደቅ ዓላማና ዓርማውን አስመልክቶ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ ምክር ቤቱን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት በቂ  ምላሽ አልተሰጠም። ጥያቄዎቹን የሚመልስ በቂ መድረክ አለመኖርና ለወጣቶችና ሌሎችም አካላት በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ ችግሩ ገዝፎ ለብጠብጠና ለሁከት መንስኤ እየሆነ ነው። በቀጣይም ምክር ቤቱና አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ሰንደቅ ዓላማን አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስና በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት እዲተገበር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የፖለቲካ ምህዳሩ በሰፋበት አገር በሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው አመለካከት ዙሪያ  በስፋት በመወያያት የጋራ ግንዛቤ መያዝ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በውይይት የዳበረውና የብሔር ብሔረሰቦችን ይሁኝታ ያገኘው ገዥ ሃሳቡ በህገ መንግስቱ ተቀባይነት እስኪያገኝ  አሁን በስራ ላይ ያለው ባንዲራ ህጋዊነቱን ጠብቆ እንዲሄድ መደረግ አለበት ብለዋል። በስነ ስርዓቱ ላይ "ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ነው ምክትል ከንቲባው ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተገኙበት በጥንታዊ አርበኞች ማህበርና በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሰልፍ ትርኢት በማድረግ የሰንደቅ ዓላማው ቀን ተከብሮ የዋለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም