በአምቦ ከተማ የገበያ ማዕከላት ግንባታ ሥራ በመጓተቱ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

104
አምቦ ጥቅምት 5/2011 በአምቦ ከተማ ከአንድ ዓመት በፊት ግንባታቸው የተጀመረው የገበያ ማዕከላት ግንባታ ሥራ በመጓተቱ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ። ለገበያ ማዕከላቱ ግንባታ ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡ ታውቋል። አስተያየት ከሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፍታሌ ዲሪባባ በሰጡት አስተያየት የማዕከሉ ግንባታ በመጓተቱ ገበያ ውስጥ የሚፈልጉትን እቃ ለማግኘት ጊዜያቸውን እያባክኑና ለእንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ወይዘሮ ይመኙሽ አበበ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው የማዕከላቱ ግንባታ የተጀመረበት ቦታ ቀደም ሲልም የገበያ አካባቢ በመሆኑ ሕብረተሰቡ እንዳይቸገር የግንባታ ሥራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል። ለእዚህም " የሚመለከተው የመንግስት አካል የተሻለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ያሉት ወይዘሮ ይመኙሻል፣ አሁን ያለው የገበያ እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመገበያየት አስቸጋሪ መሆኑን አመልክተዋል። በአምቦ ከተማ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራችው ወይዘሮ ፈትያ መሀመድ በበኩሏ ግንባታቸው የተጀመሩ የገበያ ማዕከላት በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው የንግድ ሥራቸውን ተረጋግተው ለማከናወን መቸገራቸው ገልጸዋል። የማዕከላቱ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምሩ በአሁኑ ወቅት ለዝናብ፣ ለአቧራና ለጸሐይ ተጋልጠው እያከናወኑት ያለውን የንግድ ሥራ አስቀርቶ ምቹ የንግድ ቦታ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ የከተማው አስተዳዳር ግንባታቸው የተጓተተውን የገበያ ማዕከል በፍጥነት በማጠናቀቅ የንግዱን ማህበረሰብ ችግር እንዲፈታም ጠይቀዋል። በከተማው አስተዳደር የከተማ ቤቶችና መሰረተ ልማት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ታደሰ በበኩላቸው  ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታቸው በ2009 ዓ.ም የተጀመሩት የገበያ ማዕከላት በተለያዩ ምክንያቶች እንደዘገዩ አምነዋል። ቀደም ሲል "ቶሎሳ፣ ታጠቅና ለሚሳ" በሚል ስም በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር የተደራጁ ወጣቶች በጨረታ አሸንፈው ሥራውን ቢጀምሩም በአቅም ማነስ ምክንያት ውጤታማ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። የገበያ ማዕከላቱን ግንባታ ሥራ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ቢታቀድም በተቋራጩ አቅም ማነስና የግንባታ መሳሪያዎች ዋጋ እየጨመረ መምጣት ሥራው እንዲዘገይ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራው ለሌላ ሥራ ተቋረጭ ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ከተማ የግንባታ ሥራው ከ88 ከመቶ በላይ መድረሱንም አመልክተዋል፡፡ ሥራውን ያቋረጠው ማህበርን ለህግ ለማቅረብ ተወስኖ እቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል። የገበያ ማዕከላቱ እየተገነቡ ያሉት በከተማው ቀበሌ 03 በተለምዶ አራዳ ገበያ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢና በቀበሌ 01 የገበያ ሥፍራ  እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ እንደ ሥራ እስኪያጁ ገለጻ ማዕከላቱ እየተገነቡ ያሉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የከተማውን ልማት ለማገዝ ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ ነው። የማዕከለቱ ግንባታ ሥራ በመጪው ህዳር ወር መጨረሻ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ለ250 ነጋዴዎች ምቹ የንግድ ቦታዎችን እንደሚፈጥሩ ተመልክቷል። በግንባታው ሂደት ከ400 ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ነው አቶ ከተማ የገለጹት፡፡ አቶ ከተማ እንዳሉት የገበያ ማዕከሉ መገንባት በተበታተነ ሁኔታ እየተከናወነ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ መልክ በማሲያዝ ለንግዱ እና ለሸማቹ  ማህበረሰብ የተሻለ ነገር ይፈጥራል። በተለይ ተመሳሳይ ሸቀጦችን በአንድ ስፍራ ለማግኘት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር የሸማቾችን መጉላላት እንደሚቀንስ አስታውቀዋል፡፡ የመስሪያ ቦታ ላጡ ዜጎች በገበያ ማዕከሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ለከተማ አስተዳደሩ የገቢ ማስገኛ ምንጭ በመሆን በኩልም የራሱ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም