የኢትዮ-ኩባ ግንኙነት ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም እንዲያስገኝ መስራት ይገባል-ፕሬዝዳንት ሙላቱ

87
አዲስ አበባ ጥምቅት 4/2011 የኢትዮ-ኩባ ግንኙነት ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም እንዲያስገኝ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ገለጹ። ፕሬዝዳንቱ ዛሬ የካራማራን ድል 40ኛ ዓመት ለማክበር በኢትዮጵያ ለነበሩ የኩባ ከፍተኛ ልዑክ የእራት ግብዣ አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ በፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት ኩባዊያን ወንድሞች የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ሲባል ውድ ህይወታቸውን ጭምር መሰዋታቸውን አስታውሰዋል። በዚህም የተነሳ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት የተጠናከረ ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ትልቅ ቦታ ይሰጣል ብለዋል። ሁለቱ አገሮች ካላቸው ወዳጅነት የተነሳ ኩባ የኢትዮጵያን ልማት ስትደግፍ መቆየቷን አስታውሰው፤ ከዚህም መካከል በትምህርት፣ በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የምታደርገው ድጋፍ ተጠቃሽ ነው ብለዋል። ይህንኑ እውን ለማድረግም ከ5 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በተለያዩ የኩባ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሰለጠኑ አስታውሰዋል። ይሄ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ተሻግሮ የሁለቱን አገራት ህዝቦች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲያደርግ መስራት እንደሚያስፈልግ አዕንኦት የሰጡት ፕሬዝዳንቱ፣ ለዚህም የሁለቱ አገራት ፖለቲካዊና ታሪካዊ ግንኙነት በተሻለ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲታገዝ እንሰራለን ብለዋል። የልዑኩ መሪ የኩባ መከላከያ ምክትል ሚኒስትር ጄኔራል ራሞን ኢስቲኖሳ በበኩላቸው 133 የኩባ ወታደሮች የወዳጅ አገር ኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር መሰዋታቸውን አስታውሰው፤ "እነሱ የሞቱለት የጋራ ጥቅማችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ብለዋል። ይህም እውን እንዲሆንና የሁለቱ አገራት ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኩባ መንግስት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወትም አረጋግጠዋል። የኩባ መንግስት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም