በሶማሌ ክልል በየደረጃው ያለውን አመራር መልሶ የማደራጀት ሥራ እየተጠናቀቀ ነው---ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ

78
ጅግጅጋ ጥቅምት 4/2011 የሶማሌ ክልል ሕዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በየደረጃው ያለውን አመራር መልሶ የማደራጀት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ። ምደባው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በክልሉ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል ያስችላል ተብሏል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሙስተፌ መሀሙድ ዛሬ ከጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ ምክር ቤት በዞኖችና በወረዳዎች ያሉትን መዋቅሮችን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራውን እያገባደደ ነው። ባለፉት ሁለት ወራት የክልሉ መንግሥት ዋነኛ ሥራ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከህዝቡና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መሥራት እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም በክልሉም ሆነ ከአሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች አንጻራዊ መረጋጋት መፈጠሩን ገልጸዋል። ’’በክልሉ ሰላማዊ የሥልጣን ርክክብ አልተካሄደም፤ ከባዶ ቦታ ነው የመዋቀር ሥራውን የጀመርነው፤ በዚህ ምክንያት ከተፈጠሩ ችግሮች ዋነኛው የአመራር ክፍተቱን ለመሙላት በክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ የዞን፤ ወረዳና የከተሞች አስተዳደር አመራሮች ከአድሎና ጎሰኝነት በፀዳ መልኩ ምደባ አካሄደናል'' ብለዋል። የቀድሞው የክልሉ አመራር የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮችን ከትውልድ ቦታቸው አርቆ ይመደብ እንደነበር ያመለከቱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር አመራሮች ወደ ትውልድ ሥፍራቸው በመሄዳቸው በክልሉ ቢሮዎች፣ በ11 ዞኖች፣ በ93 ወረዳዎችና በስድስት የከተማ አስተዳደሮች ክፍተቶች መፈጠራቸውን ገልጸዋል፡፡ አዲሱ የክልሉ አመራር ሕዝቡ ኢትየጵዊነቱን እንዲያጠናክርና ከጎሰኝነት ይልቅ በሶማሌነቱ እንዲያምን ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም  አቶ ሙስተፌ አመልክተዋል። ''ጎሰኝነት በተስፋፋ ቁጥር የህዝቡ እንድነት ይሸረሽራል፤ በዚህ ምክያንት በክልሉ ሥራ አጥነትን ለማጥፋትና የአርብቶ አደሩን የልማት ተጠቃሚነት ለማድረግ  አዳጋች ይሆናል'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ የታችኛው አስተዳደር መዋቅር ባይኖርም፤ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና ክልሉ ወደ ነበረበት ሰላም በመመለስ መልካም ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮቹን ለመፍታት ከአዲሱ አስተዳደር ጎን ሆኖ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ የአገሪቱ የለውጥ ሂደት የሚያራምዱ አመራሮች ምደባ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በክልሉ የልማት ሥራዎችን ለማካሄድ  እንደሚያስችልም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጧቸው አስተያየቶች የመካከለኛና የታችኛው አስተዳደር መዋቅሮች የአመራር ምልመላ በጎሳዎች መካከል ግጭትና የሥልጣን ይገባኛል ጥያቄዎች እንዳያስከትል ብሎም የመልካም አስተዳደር እጦት ምንጭ እንዳይሆን በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ በተለይ ከጎሣ መሪዎች አንዱ ገራድ አብዲ ቀኒ በክልሉ ወረዳዎች ሰላምን ለማረጋገጥና የሕዝብ  አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት በየደረጃው ያሉትን መዋቅሮች በፍጥነት ማደራጀት ይገባል ብለዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሁሴን መሐመድ በበኩላቸው የክልሉ አመራር የህዝቡን አንድነትና መረጋጋት ለማጠናከር የጀመራቸውን ሥራዎች ከዳር ለማድረስ ድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም