በእጅ የያዙት ወርቅ - - -

112

ትንሳኤ ገመቹ /ኢዜአ/

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ጥቅምት ላይ ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሄት “ማህበራዊ ሚዲያ መርዝ የመርጨት አቅም አለው” የሚል ሰፊ ትንታኔን አስነብቧል። የመጽሄቱ የፊት ሽፋን በራሱ ኤፍ የምትለው የፌስቡክ መለያ ምልክትን በመገልበጥ ሽጉጥ አድርጎ ከጫፉ ላይ ጭስ የመሰለ ጥቁር ነገር ሲወጣ የሚያሳይ ነው። የዚህ ምልክት ትርጉም ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለመልካም ስንጠቀም የሚሰጡንን ጠቀሜታ ያህል ለክፉ ነገር ስንጠቀመው መርዝ የሚረጭ፣ ሰዎችን እርስ በርስ የሚያጋጭ፣ የሌሎችን ስብዕና የሚጎዳ በዋናነት ግን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን የሚገድል መሆኑን ነው። ማህበራዊ ድረ - ገፆች ታድያ በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን የማሳደር አቅማቸው ይህን ያህል የጎላ ከሆነ አጠቃቀሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ መጽሄቱ ያትታል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ “በቀደሙት ሚዲያዎች ማለትም በቴሌቭዥን፣ ሬዲዮ፣ በጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ያለው በቡድን መረጃዎችን የማጣራት፣ ሚዛናዊነትና ትክክለኛነት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቦታ የላቸውም” ይላሉ። ለምሳሌ በቀደሙት መገናኛ ብዙሃን ሪፖርተሩ ያመጣውን መረጃ አርታኢው ትክክለኛነቱን ያጣራል፣ ሚዛናዊነቱን ይመዝናል፣ የተገኘው መረጃ በህብረተሰቡ ላይ ሊያመጣው የሚችለውን ጉዳትና ጠቀሜታ መዝኖ ዘገባው እንዲተላለፍ ይደረጋል። በማህበራዊ ድረ-ገፆች ግን ይሄ ዕድል የለም። አንድ ሰው በተሰማው ስሜት ወይም ባገኘው መረጃ ላይ ተመርኩዞ መረጃን ማሰራጨት ይችላል። በመልካምም ሆነ በጥላቻ መንፈስ ተነሳስቶ የፈለገውን እውነታውን ደብቆ ሀሰተኛ መረጃ በመፍጠር ሊያሰራጭና ጥፋት ሊያደርስ ይችላል። እንደ ዶክተር ጌታቸው ማብራሪያ ከዋናዎቹ መገናኛ ብዙሃን ቀጥሎ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ዜጎችን በአገራቸው ማንኛውም ጉዳዮች ላይ “ያገባኛል” በሚል ስሜት በነጻነት ሀሳባቸውን በመግለጽ መሳተፋቸው ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ይሁንና በማህበራዊ ድረ-ገጾችም ሆነ በዋናዎቹ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያለውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በጥንቃቄና በሃላፊነት ስሜት ካልተጠቀምንበት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የከፋ መሆኑንም ያስረዳሉ። አለም አንድ በሆነችበት በዚህ ወቅት የመረጃን ፍጥነትንና ተደራሽነትን ማንም ሊቆጣጠረው አልቻለም። በተለይ ዴሞክራሲ ጎልብቶባቸዋል የሚባሉ አገሮች ጭምር በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚተላለፉ መልዕክቶች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እየገቡ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ ከሚያቀርቧቸው መረጃዎች መረዳት አያዳግትም። በተለያዩ ድረ-ገፆች የሚተላለፉ የሀሰት ወሬዎችና የጥላቻ ንግግሮች ዴሞክራሲን ከማጎልበት ይልቅ የሚያቀጭጩ ብሎም የሚያጠፉ ናቸው።ይህን ዕድል በተቀራኒው ከተጠቀምንበት ግን “የተሻሉ ሀሳቦችን በማመንጨት የመሞገት ባህልን የሚያዳብር ነው” ይላሉ ዶክተር ጌታቸው። እነዚህ ድረ-ገጾች በተደጋጋሚ የሚያወጧቸው መረጃዎች ሀሰተኛና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ከሆነ ተዓማኒነታቸውን እያጡ ይሄዳሉ። ተጠቃሚያቸውም በዚያው መጠን እየቀነሰ ይሄዳል። ከላይ በተጠቀሰው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት ለንባብ በበቃበት ወቅት በተደረገ ጥናት በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ላይ እምነት ያላቸው የአሜሪካ ዜጎች 37 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሷል። አብዛኛው ዜጋ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች የግለሰቦችን ስም የሚያጠፋ፣ጥላቻን የሚፈጥሩና ያልተረጋገጡ በመሆናቸው እምነት አያሳድሩበትም። በአገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተርና ኢንስታግራም የመሳሰሉት ማህበራዊ ድረ-ገጾችን በመጠቀም በፋይናንስና በሌሎችም ድጋፎች እጥረት ምክንያት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አገልግሏል። ብዙ በጎ ስራዎችና አስተሳሰቦችም ለሌሎች አርዓያ ይሆን ዘንድ በነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሀሳብ ተንሸራሽሮበታል። ለአብነትም የመታከሚያ ገንዘብ አጥሯቸው በበሽታ የሚሰቃዩ ህሙማን በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚለቋቸው መረጃዎች ብዙ ድጋፎችን ማግኘት ችለዋል። ለረጅም ዓመታት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል። በሌላ መልኩ ማህበራዊ ድረ-ገጾችን ለክፉ የሚጠቀሙ ሰዎች ቅድሚያ ተጎጂ የሚሆኑት ራሳቸው ናቸው። ሁሉም የሰው ፍጡር ሰብዓዊነትን ይዞ ነው የሚወለደው። የሰብዓዊነት ስሜት እንደየሰው ይለያይ እንጂ ሰው ሰው ሆኖ ሲፈጠር ግን ይህን ስሜት ይዞ ነው። በተለይ እኛ ኢትዮጵያን በሀዘንና ደስታ አንዳችን ለአንዳችን ቀድመን የምንደርስ በአንድነታችን ውስጥ ልዩነታችን በውበት የሚገለጽ፣ የወገናችን ጉዳት የሚጎዳን፣ ህመሙ የሚጠዘጥዘን፣ ሞቱ እንቅልፍ የሚነሳን ነን። ይህን የዜጎች ለዘመናት ተከባብሮ፣  ተቻችሎና ተፋቅሮ የመኖር እሴትን ያሁኑ ትውልድ ጠንቅቆ ያውቀዋል። በዚህ ታሪክም ይኮራል። ይሁንና ይህን መልካም እሴት የራሱ አድርጎ ማሰብና መተግበር ላይ ትልቅ ክፍተት አለ። ለዚህ ደግሞ አሁን አሁን ተጋነውና ተቀነባብረው በማህበራዊ ሚዲያ የሚወጡ መረጃዎችን ማየት በቂ ነው። በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን መነሻ በማድረግ በማህበራዊ ሚዲያዎችና ድረ ገጾች የሚለቀቁ የበሬ ወለደ መረጃዎች በተለይ ወጣቱን ስሜታዊ በማድረግ አላስፈላጊ ነገር እንዲፈጽም ገፋፍተዋል። አሁንም እየገፋፉ ናቸው። በተለይ ያልተረጋገጡ መሰረተ ቢስ የሃይማኖትና ብሄር ተኮር መልዕክቶች ምክንያት በህገ መንግስቱ የተደነገገው የዜጎች በነጻነት ተዘዋውሮ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት ተጥሷል። መልካም ስማቸው ጎድፏል። ከምንም በላይ ግን ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረትም ወድሟል። የግጭቶቹ መነሻ የተለያየ ቢሆንም ለችግሮቹ መባባስ  ማህበራዊ ሚዲያና ድረ-ገፆች የራሳቸው ሚና ነበራቸው። ታድያ ችግር ሲፈጠር የችግሩን መንስኤ አጣርቶ ወደ መፍትሄው ከመሄድ ይልቅ በእሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ምን ይሉታል። በችግሩ ምክንያት የሚጎዳው የሌላ አገር ዜጋ ሳይሆን የራሳችን ወገን መሆኑስ ይዘነጋ ይሆን? በማህበራዊ ሚዲያው ያገኘነውን ዕድል ተጠቅመን አገርንና ወገንን ለመጥቀም የሚያስችል ተግባር ማከናወን ስንችል “በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” እንዲሉ ካሁኑ ቆም ብለን ማሰቡ የተሻለ ይሆናል። እኤአ በ2011 በወጣው መረጃ በኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አንድ በመቶ ህዝብ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ ከ60 በመቶ በላዩ ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 30 ያሉ ወጣቶች ናቸው። ባለፈው መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በፓናል ውይይት ተከብሯል። በዚሁ ወቅት ተሳታፊ የነበረው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ማህበራዊ ሚዲያን አስመልክቶ ባቀረበው ሃሳብ ዋናው ሚዲያ በመረጃ ነጻነት ላይ በትክክል አለመስራቱ እውነትንና እውቀትን ማጣጣም ያልቻለ የማህበራዊ ሚዲያ እንዲፈጠር ማድረጉን አጽንኦት ሰጥቶታል። ዋናው ሚዲያ በመረጃ እጥረት፣ በአቅም ክፍተት፣ መረጃን በወቅቱ ባለማግኘት የተነሳ ማህበራዊ ሚዲያው የሰዎችን ቀልብ የሳበበት ምክንያት መፈጠሩንም ነበር ያስረዳው። በፈጣን እድገት ላይ ካለው የቴክኖሎጂ እድገት ጋር አብሮ የሚሄድ የመረጃ ህግ እስካልተፈጠረ ድረስ በቀጣይም ማህበራዊ ሚዲያው ዋናውን ሚዲያ መምራቱ አይቀሬ መሆኑን ዲያቆን ዳንኤል አጽንኦት ሰጥቶታል። በኢትዮጵያ የሚዲያና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ቀደም ሲል ከነበረው እየተሻሻለ መምጣቱን ይህንንም የበለጠ ለማጠናከር የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት አዋጁ እንደሚሻሻል የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በህዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2011 ዓ.ም የስራ ዘመን መክፈቻ ላይ መናገራቸው አይዘነጋም። ፕሬዝዳንት ሙላቱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የህብረተሰቡን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት በሚያጠናክር ስሜት መረጃውን እንዲያስተላልፉና እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። ታድያ በማህበራዊ ድረ-ገፆች ያገኘነውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተጠቅመን ለአገሪቷ ዴሞክራሲ ግንባታ የበኩላችንን አሻራ ብናሳርፍ ምን ይለናል?
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም