በአፋር ክልል ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሕብረተሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ ነው...የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን

120
ሰመራ ግንቦት 13/2010 በአፋር ክልል ያለው ሰላም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ሰሞኑን በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች የሰላም እጦት እንዳለ ተደርጎ የሚነዛውን ወሬ ከእውነት የራቀ ተራ አሉባልታ መሆኑን ተናግረዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሸን ኮሚሽነር አሎ አፍኬኤ እንደተናገሩት ረሺድ ሳልህ የተባለ የክልሉ ነዋሪ በህዳር ወር 2010 ዓ.ም መጨረሻ ድንገት መጥፋቱን ተከትሎ ከቤተሰቦቹ ለፖሊስ መረጃ ደርሷል። በተደረገው ማጣራት በክልሉ ጸጥታ አካላትና እስር ቤቶች ውስጥ ግለሰቡ አለመኖሩን በተለያዩ ጊዜያት ለቤተሰቦቹና ለሕብረተሰቡ ማረጋገጫ እንዲሰጥ ተደርጓል። ይሁንና ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎችና አካባቢዎች ሁከትና ግርግር እንደተፈጠረ ተደርጎ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተነዛው ወሬ ከተራ አሉባልታነት የዘለለ አለመሆኑን ተናግረዋል። እንደ ኮሚሽነር አሎ ገለጻ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ጧት ላይ "እረሺድ ሳልህ ይፈታ" የሚል ወረቀት በግቢው ውስጥ ተለጥፎ ተገኝቷል። ከዚህ ጋር ተያየዞ ሁለት ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ሥራ እየተከናወነባቸው መሆኑን አስረድተዋል። የክልሉ ሰላም ወዳድ ሕብረተሰብ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በሰለጠነ መንገድ በውይይት የመፋታት ባህላዊ እሴቱን ከመጠበቅ ባለፈ  ከክልሉ መንግስትና የጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቆም ለክልሉ ሰላምና እደገት የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናክርም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል። የሰሜን ምስራቅ እዝ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊና የቀጠና 6 ኮማንድ ፖስት አባል ኮሎኔል ሐጎስ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የኮማንድ ፖስት አደረጃጀቶች ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። "በእዚህም ክልሉ የገነባውን ጠንካራ የሰላም እሴት ይበልጥ አጎልብቶ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ብለዋል። እንደ ኮሎኔል ሐጎስ ገለጻ፣ በተለይ ዋነኛ የአገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ የሚንቀሳቀስበት የትራንስፖርት መስመር ምንም የጸጥታ ችግር እንዳይገጥመው ኮማንድ ፖስቱ ከወረዳና ዞን አመራሮች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል። የክልሉን ሰላም አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው እስካሁን የሰላም እጦትም ሆነ የጸጥታ መደፍረስ ችግር በክልሉ አለመከሰቱን ተናግረዋል። በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተለጥፎ የተገኘውን ወረቀት አስመልክቶም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ አመራርና ሠራተኞች በተገኙበት የጋራ ውይይት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም