ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካን መርቀው ከፈቱ

64
አዲስ አበባ ጥቅምት 4/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ መርቀው ከፈቱ። በ8 ቢሊዮን ብር በተገነባው በዚሁ ፋብሪካ የምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኤርትራው ፕሬዝዳንት አማካሪ የማነህ ገብረአብ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የቻይና ልማት ባንክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ቡ ዪ እንዲሁም የደቡብ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትም ተገኝተዋል። ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘው 8 ቢሊዮን ብር ብድር የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ ተቋራጭነት የተገነባ ሲሆን የሙከራ ምርቱን ዛሬ ይጀምራል። ፋብሪካው የሙከራ ስራውን የሚጀምረው ከ2ሺህ እስከ 3ሺህ ቶን ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ነው። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር በቀን ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን የአለም ገበያን ፍላጎት መሰረት በማድረግም ጥሬ ስኳር፣ ነጭ ስኳር እና የተጣራ ስኳር ማምረት ይችላል። ከሁለት ወር በፊት በተደረገው ፍተሻ የፋብሪካው ማምረቻ ማሽኖች  ወደ ምርት ለመሸጋገር ዝግጁ መሆናቸው ተረጋግጠዋል። በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር በሚገኙ አራቱም ፋብሪካዎች በ100 ሺህ ሄክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የመስኖ መሰረተ ልማት ተከናውኗል፤ እስካሁንም ባለው ሂደት 30ሺህ ሄክታር መሬት የመስኖ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል። የመስኖ ውሃ ካገኘው መሬት ውስጥም 16ሺህ ሄክታር በሚሆነው መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ መተከሉም ተገልጿል። የአሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ወደ ምርት በተሸጋገረበት መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ፋብሪካ ግንባታ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። ፕሮጀክቱ ወደ አገልግሎት መግባቱ በአገሪቱ ስኳር ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ ስምንት ያደርሰዋል። በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር ከሚገነቡት አራት የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው ይህ ፋብሪካ፤ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑት በከፋና ቤንች ማጂ ዞኖች መሃል ይገኛል። ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ110 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ከስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም