የተለያዩ የግብርና ምርት ማሻሻያ ዘዴዎችን በመተግበራቸው ውጤት እያመጡ እንደሆነ አርሶ አደሮች ገለጹ

78
አምቦ ጥቅምት 3/2011 በኩታ ገጠም ማሳ በመዝራትና የግብርና ግብዓት በመጠቀም በምርትና ምርታማነታቸው ላይ ውጤት እያመጡ እንደሆነ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጣይባ ሀሰን የተመራ ቡድን በወረዳው የሚገኙ በኩታ ገጠም ማሳ የተዘሩ የተለያዩ ሰብሎችን፣ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ እና ምርት ማላመድ ስራዎችን ጎብኝቷል። በጉብኝቱ ወቅት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች እንደገለጹት፤ በኩታ ገጠም ማሳ ሰብሎችን በመዝራትና የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በመጠቀማቸው ምርትና ምርታነታቸው ጨምሯል። በግብርና ባለሙያዎች በሚሰጣቸው ስልጠና መሰረት የተለያዩ የግብርና ምርት ማሻሻያ ዘዴዎችን መተግበራቸው ውጤታማ እያደረጋቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል። ከዚህ በፊት በሄክታር 26 ኩንታል ብቻ ያገኙ የነበሩት አርሶ አደሮቹ እስከ 58 ኩንታል የሚደርስ የስንዴ ምርት እያገኙ እንደመጡ ጠቁመዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ዓመት በወረዳው ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምባይነር የስንዴ ምርት መሰብሰብ ጀመረዋል። አርሶ አደር ሙለታ ዱጉማ  በሰጡት አስተያየት˝በክላስተር በመዝራታችን ምርትና ምርታማነታችንን ለማሳደግ ረድቶናል፣ የግብርና ባለሙያዎች በሰጡትን ትምህርት መሰረት በህብረተ በመደራጀት ደጋግገመን በማረሳችን ከግማሽ ሄክታር ላይ 29 ኩንታል አግኝተናል፣ ከአንድ ሄክታር ደግሞ 59 ኩንታል ስንዴ አግኝተናል" ብለዋል፡፡ ሌላው አርሶ አደር ሙለታ ገቢሳ በበኩላቸው ጤፍን በመስመር የመዝራትና ስንዴን በቢቢኤም ማረሻ እንዲሁም የተለያዩ የአፈር መዳበሪያ በጠቀም ምርትና ምርታነታቸው እየጨመረ መሆኑን ይገልጻሉ። "ጤፍን በመስመር በመዝራት፣ ስንዴን በቢቢኤም ማረሻ በመዝራት፣ ከጥቁር አፈር ውሃ በማጠንፈፍ፣ ምርቱ በአግባቡ እንዲያፈራ ረድቶናል፣ በሄክታር ብዙ ለውጦች እየመጡ ነው ፤ጤፍ በሄክታር እስከ 19 ኩንታል ምርት ይገኛል "ያሉት ደሞ  አርሶ አደር ጉታ ገቢሳ ናቸው፡፡ በወረዳው የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ ገመቹ ቡልቶ በበኩላቸው በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ምርጥ ዝርያዎችን የማላመድ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የዝርያዎቹን ውጤታማነት በማየት ወደአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭም ገልጸዋል። የጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሽንብራ እና የሌሎች ሰብሎች ምርጥ ዘር ከአየር ንብረቱና ከአካባቢው አፈር ጋር የማላማድ ስራዎች በማሰልጠኛ ማዕከላቱ እንደሚከናወን ጠቁመዋል። በኩታ ገጠም ማሳ የመዝራትና እርሻውን የማዘመን ስራ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ እየተሰራ እንደሚገኝም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጣይባ ሀሰን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ የሚቀርብለትን የቴክኖሎጂ አማራጭ ተቀብሎ በመተግበሩ ምርታማነቱን እያሳደገ እንደሆነ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ምርታማነቱን በማሳደግ ኑሮውን ከማሻሻል ባለፈ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያስችለው የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያገኝ ስትራቴጂ ተቀርጾ እንደሚሰራ ወይዘሮ ጣይባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም