አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና-ፍኖተ ካርታ ለአገር ዕድገትና ተወዳዳሪነት የሚተጋ ትውልድ ለማፍራት አጋዥ መሆኑ ተጠቆመ

152
ድሬዳዋ ጥቅምት 3/2011 አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና-ፍኖተ ካርታ ለአገር ዕድገትና ተወዳዳሪነት የሚተጋ ትውልድ ለማፍራት አጋዥ መሆኑን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ተናገሩ፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና-ፍኖተ ካርታ ላይ ተወያይተዋል፡፡ የውይይቱ ሳታፊ  የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ስራ ላይ ያለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በየደረጃው ባሉ የትምህርት እርከኖች ባግባቡ ባለመተግበሩ አገሪቱ በምትፈልገው ደረጃ ብቁ የሆነ የተማረ ኃይል ማፍራት አልተቻለም፡፡ ፖሊሲው በመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት እርከን ላይ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማራቸው ጥሩ ቢሆንም ተጨማሪ ቋንቋ በመማር በቀጣይ ህይወታቸውና  በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማስቻል አንጻር ውስንነት ያለው መሆኑን መምህራኑ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና-ፍኖተ ካርታ አሁን በስራ ላይ የለውን የስልጠናና የትምህርት ፖሊሲ መሰረታዊ ችግሮችና መፍትሄዎችን ማመላከት መቻሉ በጥሩ ጎኑ የሚያስጠቅሰው መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸው የሁለት አገራትን ተሞክሮ ብቻ መውሰዱ ግን በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፍኖተ ካርታው የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቆይታ አንድ ዓመት እንዲጨምር ማመላከቱ አግባብ መሆኑን የገለጹት መምህራኑ፣ ከዘመኑ ጋር  የሚመጣጠን የአገሪቱንና የአለምን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ እውቀትና ክህሎት ማስጨበጥ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የግል ትምህርት ቤቶች በራሳቸው ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸው ማስተማራቸው እየፈጠረ የሚገኘውን ችግር ፍኖተ ካርታው በተጨባጭ ፈትሾ ሊያሳይ እንደሚገባም የውይይቱ ተሳታፊዎች አመልክተዋል፡፡ እንደተሳታፊዎቹ ገለጻ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምህራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፈርት መሠረት አስተማሪዎችን ሊቀጥሩና በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉበትን አግባብ በሚያመልክት መልኩ ፍኖተ ካርታው ሊቃኝ ይገባል፡፡ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አባያ ደገፈ ውይይቱ በጣም ጥሩና ቀጥታ ከሙያ ጋር የተገናኘ መሆኑን ገልጸዋል። አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በትምህርት ጥራት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ላይ ያሉ ችግሮችን ሥር ነቀል በመሆነ መንገድ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ "በውይይቱ የተገኘው ግብዓት በቀጣይ በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ሲካተት የመምህራን ቅጥርን፣ ጥቅማጥ ቅሞችንና የደመወዝ ችግሮችን የሚፈታና በመማር ማስተማሩ ላይ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሚያግዝ ነው" ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ነጻነት ሽፈራው  አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ በተጨባጭ የሚታዩ  ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው በመማር ማስተማሩ ሂደት በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ የሚያሳይና ችግሮች በዘላቂነት ተፈተው ትውልዱን ለአገር እድገት ወሳኝ እንዲሆን አድርጎ መቅረጽ የሚያስችል ነው" ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ መምህር አንዶም በርሄ ናቸው። ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለፍኖተ ካርታው የሚያግዝ ግብዓት መገኘቱን ገልጸዋል። "አዲሱ የትምህርትና ስልጠና-ፍኖተ ካርታ የጥናት ውጤት ብቁና በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሃዊነትና ጥራትን ለማረጋገጥ የሚኖረው አስተዋጽ የጎላ ነው" ብለዋል፡፡ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊና ሥነ ሰብ ትምህርት ክፍል ዲን የሆኑት ዶክተር እንዳወቅ አበበ በበኩላቸው በፍኖተ ካርታው የተቀመጡ አቅጣጫዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ ተቀናጅቶና ተናቦ የመሄድ ችግሮችን ትርጉም ባለው መልኩ መፍታት የሚያስችሉ ሆነው እንዳገኟቸው ገልጸዋል፡፡ ለዘመኑ የሚመጥን እውቀትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ከማገዝ አንጻር ፍኖተ ካርታው የላቀ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ዶክተር እንዳወቅ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም