በትምህርታቸው ውጤታማ በመሆን ሰንደቅ አላማው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተማሪዎች ተናገሩ

54
ጥቅምት 3/2011 በትምህርታቸው ውጤታማ በመሆን አገራቸውን በማስጠራት ሰንደቅ አላማው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ በመዲናዋ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተገኝቶ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተማሪዎች እንዳሉት ሰንደቅ አላማው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና እንዲከበር  ሁሉም መረባረብ ይገባዋል፡፡ የዳግማዊ ሚኒሊክ መሰናዶ የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ነጃት መካ እንደተናገረችው ሰንደቅ አላማ የሃገርና የህዝብ የአንድነት መገለጫና ማንነት በመሆኑ ከፍተኛ ክብር ሊሰጠው ይገባል ፡፡ ሁሉም ተማሪ በሰንደቅ አላማው በመኩራት  ሲሰቀል  የአገሩን መዝሙር በፍቅር እየዘመረ መሆን እንዳለበትም ገልጻለች፡፡ ጠንክራ በመማርና ውጤታማ በመሆን የአገሯ  ሰንደቅ አላማ በዓለም አደባባይ ከፍ እንዲል ያላትን  ፍላጎት አስረድታለች ፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ሰንደቅ አላማው አርጅቶ ተሰቅሎ መታየቱ ትክክል አለመሆኑን የተናገረችው  የዚሁ ትምህርት የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ምኞት ሃይሌ በበኩሏ ለሰንደቅ አላማው አስፈላጊውን ክብር በመስጠት ተማሪዎች ሰንደቅ አላማውን እንዲያከብሩና አገራቸውን እንዲወዱ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክታለች፡፡ በየሃ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አካዳሚ የ11ኛ ክፍል ተማሪው ቅዱስ ሳምሶን በስነ- ዜጋ ትምህርት ስለ ሰንደቅ አላማ በቂ ግንዛቤ እንዳገኘ ጠቅሶ በቀጣይ በተጠናከረ ሁኔታ መሰጠት እንደሚገባው አመልክቷል ፡፡ ሰንደቅ አላማ የአንድ አገር መገለጫ በመሆኑ ሁሉም በአንድነት ሊቆምለት ይገባልም ብሏል ፡፡ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት በተያዘው የትምህርት ዘመንም ተማሪዎች በሰንደቅ አላማ ላይ ያላቸው ግንዛቤ የበለጠ እንዲያድግ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ፡፡ በሰንደቅ አላማ ዙሪያ የሚነሱ ብዥታዎችን መፍታት በሚያስችል ሁኔታ የፓናል ውይይት በማድረግ 11ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደሚከበርም ጠቁመዋል ፡፡ 11ኛውን የሰንደቅ አላማ ቀን በትምህርት ቤታቸው በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ የቀለመ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወይዘሮ አዲስ አለም ታዬ ናቸው ፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሰንደቅ አላማው ዙሪያ የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራት  በቀጣይ መንግስት  ሰፊ ውይይት መፍጠር  እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡ የዘንድሮው የሰንደቅ ዓለማ ቀን “ሰንደቅ አላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ለ11ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም