የጅማ ዩኒቨርሲቲ አዲስና ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

66
ጅማ ጥቅምት 3/2011 የጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2011  የትምህርት ዘመን አዲስና ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታዬ ቶለማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ  በአሁኑ ወቅት  አዲስና ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የዝግጅት ሥራውን አጠናቋል፡፡ በ250 የተለያዩ የትምህርት መርሀግብሮች 42 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ያለው የጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2011 የትምህርት ዘመን በሰባት አዳዲስ የትምህርት መርሀ ግብሮች ተማሪዎችን እንደሚቀበል ታውቋል፡፡ ፕሮፌሰር ታዬ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በአዲሱ የትምህርት ዘመን 4 ሺህ 893 አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል። ከመምህራን ምደባ በተጨማሪ የተማሪዎች የመማሪያ፣ የማደሪያ፣ የመመገቢያ፣ የቤተ መጻህፍትና  የላቦራቶሪ ክፍሎችን ማደራጀት ስራን ጨምሮ ለመማር ማስተማሩ አገልግሎት አጋዥ የሆኑ ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተከናውነው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ በለቀቁ መምህራንና ሰራተኞች ምትክ በቴክኖሎጂ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ የሚያስተምሩ መመህራንን በቅጥር ለማሟላት ጥረት ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ወደዩኒቨርሲቲው የሚመደቡ አዲስ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና ላልተፈለገ አጋላጭ ባህሪ እንዳይጋለጡ ከተማሪዎች ህብረት፣ ከጅማ ከተማ አስተዳደርና ከተማሪዎች አገልግሎት ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት መታቀዱንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ "ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በሚመጠበት ጊዜ ለአዲስ ተማሪዎች የትራንስፖርት አቅርቦትን ጨምሮ የአቀባበል ሰነ ሥርዓት ይዘጋጃል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም