ግጭቶችን በዘላቂነት ለመከላከል በወጣቱ ዘንድ አገራዊ አንድነት እንዲፈጠር ጥረት ሊደረግ ይገባል ተባለ

67
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2011 በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን አለመግባባቶችና ግጭቶች በዘላቂነት መከላከል የሚቻለው አገራዊ የአንድነት ስሜትን የተላበሰ ትውልድ በመፍጠር ነው ተባለ። ይህ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ ከሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ብዙ እንደሚጠበቅ ታዋቂ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዜጎች መካከል እየተስተዋሉ ያሉት ግጭቶች የህይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመትንና መፈናቀልን እያስከተሉ ናቸው። ለዚህ ክስተት የተለያዩ ቆስቋሽ ምክንያቶች ሊጠቀሱ የሚችል ቢሆንም የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችና የአገራዊ አንድነት ስሜት እያሽቆለቆለ መምጣቱ በዋናነት ይነሳሉ። ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ሥራ የሚፈጥር ምጣኔ ኃብትን መገንባትና ተጠያቂነት የሰፈነበትን የመልካም አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያዊ አንድነትንና ብሄራዊ ስሜትን በተለይ በወጣቱ ዘንድ ማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ ጉዳይ ብዙዎች ይስማማሉ። ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዋቂ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች እንደሚሉትም ወጣቶች ስለኢትዮጵያዊ አንድነትና የህዝቦች በጋራ መኖር እሴቶችን በተመለከተ የተጨበጠ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ እስካሁን  የተደረገው ጥረት ጉድለት አለበት። የተለያየ ባህል፣ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ ባላቸው መላው ኢትዮጵያዊያን መካከል ጠንካራ አንድነት፣ ፍቅርና መተሳሰብ መፍጠር የበለፀገች አገርና ደስተኛ ህዝብ ለመፍጠር ወሳኝ  መሆኑንም ይናገራሉ። በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን በእራሳቸው ዜጎች ላይ እየፈጸሙት ያሉት ተግባር የስነ-ምግባር፣ የእምነትና የሞራል ችግር ምንጮች ናቸው ይላሉ የኢትዮጵያ የሙስሊሞች የጋራ ተቋማዊ ለውጥ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አቡበከር መሐመድ። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ስነ-ምግባር የተላበሰ ዜጋ ለመቅረጽ ከሃይማኖት መሪዎችና ከአገር ሽማግሌዎች ብዙ ይጠበቃል ባይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ዜጎች የገጠሟቸውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ በመሆናቸው ለቀጣይነታቸው መረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊያበረክት እንደሚገባም ነው አቶ አቡበከር ያስገነዘቡት። በአገሪቱ የስራ እድልን፣ የፍትህና ዲሞክራሲ ተቋማት ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለ በበኩሏ በቅርብ ዓመታት ውስጥ  ከኢትዮጵያውያን ባህልና ለዘመናት ተጠብቀው ከቆዩ እሴቶች ውጭ የሆኑ ግጭቶችና መፈናቀል እየተከሰቱ ያሉት "ለረጅም አመታት ለልጆቻችን ስለ ኢትዮጵያዊነት ያላስተማርን በመሆኑ ነው" ትላለች። በመሆኑም "ወጣቶችን ከመውቀሳችን በፊት ስለ ኢትዮጵያውነት፣ ስለ አንድነትና ፍቅር ማስተማርን የቤት ስራችን ልናደርገው ይገባል" በማለትም ታስገነዝባለች። ወጣቶች ከብጥብጥና ሁከት ርቀው አገር የመረከብ ትልቅ ራዕይ እንዲሰንቁና ማህበረሰቡም ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነቱን እንዲወጣም  መክራለች። በቅርቡ በአገሪቱ የተጀመረውን የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ጎዞ ለማስቀጠል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም ተናግራለች። የሃይማኖት አባቱ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ በበኩላቸው አንድነት ከሌለ ልማት የማይኖር በመሆኑ ወጣቶችን ስለ አንድነት፣ ሰላምና ልማት መምከር ይገባል ይላሉ። ሕብረተሰቡም የመሪዎችን ትዕዛዝ ማክበርና መተግበር እንደሚገባው እያስተማሩ መሆናቸውንም እንዲሁ። የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ኃላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች ለወጣቶች አርአያ መሆን እንደሚገባቸውና ያለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዲወጡም ሀጂ ኡመር ኢድሪስ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም