ጠንካራና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ተዘጋጅተናል-ኅብረቱ

61
አዲስ አበባ  ጥቅምት 3/2011 ጠንካራና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ኅብረት ገለጸ። የኅብረቱ አመራሮች ዛሬ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጸጋዬ ማሞ ተቀብለዋቸዋል። አቶ ጸጋዬ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ለአገር ግንባታ እንዲሰሩ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል። ''በጋራ የምንገነባው አገር እንጂ በጠላትነት የምንተያይበት ዘመን ማብቃት አለበት'' ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኅብረቱ ይህንን ጥሪ ተቀብሎ በሠላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ መምጣቱን አድንቀዋል። የአገሪቷን ልማት ለማረጋገጥ ኅብረቱ የሚያመጣውን ሀሳብ መሰረት በማድረግ በጋራ ለመስራት መንግስት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። የኀብረቱ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ገብረሚካኤል በበኩላቸው በኢትዮጵያ እያታየ ያለው ለውጥ እንዲመጣ መስዋዕትነት ለከፈሉ ወገኖች ምስጋና አቅርበዋል። ዴሞክራሲ እንዲመጣና ጠንካራ ኢትዮጵያን  መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከህዝብ ጋር የሚወያዩ እንደሆነ ጠቁመዋል። እንደ ሰብሳቢው ገለጻ ኅብረቱ አንድ አይነት ዓላማ ካላቸው ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ኢዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና ይወጣል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ፤ "ከኢህአዴግ ፓርቲ ውጪ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፤ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድምና አማራጭ ሃሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ፣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው" ማለታቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ አሸናፊ ሃሳብ ለማቅረብና አገሪቱን ወደፊት ለማራመድ በመዘጋጀት ወደአገር መግባታቸው ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም