ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ በነገው እለት የሙከራ ምርት ይጀምራል

171
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2011 የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ በነገው እለት የሙከራ ምርት እንደሚጀምር ስኳር ኮርሬሽን አስታወቀ፡፡ በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር ከሚገነቡት አራት የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው ይህ ፋብሪካ፤ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑት በካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች ይገኛል። ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ 8 ቢሊዮን ብር ብድር የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ ተቋራጭነት የተገነባ ነው። በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፋብሪካው የሙከራ ስራውን የሚጀምረው ከ2ሺህ እስከ 3ሺህ ቶን ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ነው። ከሁለት ወር በፊት በተደረገው ፍተሻ የፋብሪካው ማምረቻ ማሽኖች  ወደ ምርት ለመሸጋገር ዝግጁ መሆናቸው መረጋገጡንም አቶ ጋሻው አስታውሰዋል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር  በቀን ከ8ሺህ እስከ 10ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም እንደሚኖረው ጠቁመዋል። ፋብሪካው የአለም ገበያን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ጥሬ ስኳር፣ ነጭ ስኳር እና የተጣራ ስኳር ማምረትም እንደሚችልም አውስተዋል። ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር በሚገኙ አራቱም ፋብሪካዎች በ100ሺህ ሄክታር ላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የመስኖ መሰረተ ልማት እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጋሻው፤ "እስካሁንም ባለው ሂደት 30ሺህ ሄክታር መሬት የመስኖ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል። የመስኖ ውሃ ካገኘው መሬት ውስጥም 16ሺህ ሄክታር በሚሆነው መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ መተከሉን ገልጸዋል። የአሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ወደ ምርት በተሸጋገረበት መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ፋብሪካ ግንባታ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። ፕሮጀክቱ ወደ አገልግሎት መግባቱ በአገሪቱ ስኳር ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ ስምንት ያደርሰዋል፡፡ ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከተቋቋመ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከ110ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ከስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም