ፖሊሲና ስትራተጂው ብቁና በፈጠራ ክህሎት የተካነ የሰው ሃይል ለማፍራት ያስችላል ተባለ

62
አዳማ ግንቦት 13/2010 አዲስ የተዘጋጀው የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብቁና በፈጠራ ክህሎት የተካነ የሰው ሃይል በማፍራት አገሪቱን በምርትና አገልግሎት ተወዳዳሪ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተገለፀ ። ለፖሊሲውና ስትራተጂው ማጎልበቻ ግብአት ለማሰባሰብ የሚያስችል የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የአገራዊ የሰው ሀብት ፖሊሲና ስትራቴጂ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መንግስቱ ይትባረክ በውይይቱ መክፈቻ  እንዳሉት የተለያዩ አገራት ከድህነት ወደ ብልፅግና መሸጋገር የቻሉት የሰው ሀብታቸውን በሚገባ በማልማታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከወቅቱ ጋር የሚሄድና በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ የምትፈልግበት ምእራፍ ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል ። የተዘጋጀው ፖሊሲውና ስትራቴጂም በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት ለመሙላትና ብቁና በፈጠራ ክህሎት የተካነ የሰው ሀይል በማፍራት አገሪቱን በምርትና አገልግሎት ጠንካራ ተወዳዳሪ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል፡፡ ጠንካራ ተወዳዳሪነት ማምጣት የሚቻለው ህዝቡን፣ መንግስትንና የግል ዘርፉን በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ብቁ ሆነው ክፍተቶችን ለመሙላት ሲረባረቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አዲስ የተዘጋጀው ፖሊሲውና ስትራተጂም ይህንኑ ለማስፈፀም ያለመ መሆኑን ተናግረዋል ። ባለፈው አንድ ዓመት በዝግጅት ላይ የነበረው የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ይበልጥ ለማጎልበት ከተለያዩ አካላት ግብአት የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የፖሊሲውና ስትራተጂው ዝግጅት የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ዶክተር አበራ ደምስ በበኩላቸው ''የበለፀጉ አገራት ዋናው የእድገት ምጥቀት  በሰለጠነ የሰው ሃይል የተገኘ ነው'' ብለዋል። ከውጭ የደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር ልምድ ታሳቢ ተደርጎና የአገር ውስጥ ተሞክሮን አጣቅሶ  የተዘጋጀው ፖሊሲና ስትራቴጂው ብቁ እውቀትና ክህሎት ያለው ፣ ችግር ፈቺ ፣ በመልካም ስነምግባር የታነፀና ህዝባዊ አስተሳሰቡ ከፍ ያለ የሰው ሃይል በብዛትና በጥራት ለማፍራት ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል ። በውይይቱ ላይ ከኦሮሚያና አዲስ አበባ የመጡ የሲቪክ ማህበራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም