በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የፓለቲካ ፓርቲዎች እንቅሰቃሴ ማድረግ ፈጽሞ አይፈቀድም …ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ

117
አዲስ አበባጥቅምት 3/2011 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ፓለቲካዊ ተግባርና የፓርቲ እንቅሰቃሴ ማድረግ ፈጽሞ የማይፈቀድ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ። ክልከላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የሚያካትት እንደሆነም ጠቁመዋል። የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮ ዓመት ሰላማዊ የመማር ማስተማርን ለማረጋገጥ የሚያስችል ውይይት ከሐይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ አንዳንድ ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አዳዲስ ተማሪዎች ሲገቡ የፓርቲ አርማና ባንዲራ ይዘው የፖለቲካ ተግባራትን ያከናውናሉ። ነገር ግን በየትኛውም መመዘኛ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ መግለጫ የሆነ አርማ ይዞ መንቀሳቀስ የማይፈቀድ መሆኑን ገልጸዋል። ግለሰቦች የፖለቲካ አባልነታቸውንና አመለካከታቸውን ይዘው የመደገፍ መብታቸው የተረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አባል መመልመልና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ አይደለም  ብለዋል። መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን በማሰብ ከዚህ በፊት ሰዎች ይመድብ እንደነበረ አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ህግና ስርዓቱ ስላማይፈቅድ አሰራሩ እንዲቀር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። ስለሆነም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በተቋማቸው ያሉትን አደረጃጀቶችና የተማሪ ህብረቶችን በማጠናከር መስራት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች  የምርምር፣ የፈጠራ፣ የሥራ ፈጠራ፣ የኢንዱስትሪያላይዜሽንና የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ተግባራዊ የሚደረጉበት እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል። ተቋማቱ የለውጥ፣ የተስፋ፣ ተፈጥሮን የበለጠ ለማወቅና ለመመራመር ጥናት የሚደረጉባቸው፣ የአገሪቷን በጎ የታሪክ ገፅታና እሴቶች የሚሰፉበትና የተዛባ የነበረ ካለም የሚማሩበትና ምክንያታዊነት የሚጎለብቱበት ተልእኮ ይዞ የሚሰራባቸው እንዲሆኑ መትጋት የሚያስፈልግ እንደሆነም ገልጸዋል። በመላው አገሪቷ የሚገኙት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስና ነባር ተማሪዎችን ለመቀበል ከሐይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም