የመልካም አስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች በፌደራሊዝም ስርአቱ የታዩ ተግዳሮቶች ናቸው---የፌዴሬሽን ምክር ቤት

75
ዲላ ጥቅምት 3/2011 የመልካም አስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች በፌደራሊዝም ስርአቱ የታዩ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሀመድ ረሺድ አስታወቁ ። የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦችን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ አውደ ጥናት ትላንት በዲላ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሀመድ ረሺድ በወቅቱ እንደገለጹት የፌደራል ስርአቱ ያበረከታቸው መልካም ጎኖች ቢኖሩም የመልካም አስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች ተግዳሮት ሆነው ቆይተዋል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተግዳሮቶቹን ተከትሎ በተከሰቱ ግጭቶች የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀል፣ የአካልና ሥነ-ልቦና ጉዳት እንዲሁም የንብረት መውደም አደጋ ደርሷል። የዜጎች ተዘዋውሮ የመስራት፣ ንብረት የማፍራትና የመሳሰሉ ሕገ-መንግስታዊ መብቶችም መጣሳቸውን ነው የገለጹት፡፡ "ግጭት በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ የሚኖር ተፈጥሯዊ ክስተት ነው" ያሉት አቶ መሀመድ ከመደበኛ ግጭት መፍቻ ተቋማትና ሥርዐቶች በላይ ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን መጠቀም የተሻለ መግባባትና መረዳዳትን ለመፍጠር አስተዋጾ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል ። የጌዴኦና የጉጂ ዞን ህዝቦችም ባህላዊ የግጭት መከላከልና አፈታት እሴቶችን በማጎልበትና ጥቅም ላይ በማዋል ማህበራዊ ትስስሮቻቸውን በማጠናከር ዘላቂ ሠላምና ልማት ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል ። የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ከዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር በማህበረሰብ ውስጥ ያሉ መልካም እሴቶቹን ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን አቶ መሀመድ አስታውቀዋል ። የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ታደሰ በበኩላቸው ግጭቶች ሲከሰቱ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ ቀድሞ መከላከል ከተከሰተ በኋላም ዳግም እንዳያገረሹ በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ አስረድተዋል ፡፡ በቅርቡ በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በጌዴኦ ዞን አጎራባች አካባቢ ተከስቶ የነበረው ግጭት ጥቂት ግለሰቦች የጠነሰሱት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው "ክስተቱ ሰፊውን ህዝብ በማሳተፍ ለጋራ ሠላምና እድገት መስራት እንደሚገባን አስተምሮናል" ብለዋል ። በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የግጭት አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ገልቹ ጃርሶ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የጌዴኦና ጉጂ ኦሮሞ ህዝቦችን አንድ ከሚያደርጓቸው ባህላዊ ክዋኔዎች መካከል በሁለቱም ህዝቦች ዘንድ "ጎንዶሮ" በመባል የሚታወቀው የእርቅ ሥርዐት ተጠቃሽ መሆኑን አመላክተዋል። የእርቅ ስርአቱ በህዝቦች መካከል ማህበራዊ ትስስር ሳይቋረጥ እንዲቀጥልና እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሌላው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ በጌዴኦ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የባህል ታሪክና ቅርስ ጥናትና ልማት ቡድን መሪ አቶ ፀጋዬ ታደሰ ናቸው። አቶ ታደሰ የ"ጎንዶሮ" ሥርዐት ሁለቱ ህዝቦች ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙበት የቆየ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግጭቶችን ለመፍታትና ግጭት ውስጥ የገቡትን ለማቀራረብ የሚረዳ ባህላዊ እሴት መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ ባህላዊ እሴቱን በማጎልበት ለግጭቶች ዘላቂ መፍቻ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት አስተዳደራዊ እገዛን እንደሚያሻ አመላክተዋል ። በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና በደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ትብብር በተዘጋጀው አውደ ጥናት የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት፣ የምዕራብና ምስራቅ ጉጂ እንዲሁም የጌዴኦ ዞኖች አመራር አካላት፣ አጋር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም