ዩኒቨርሲቲዎቹ የመማር ማስተማር ሂደቱ ያለምንም ስጋት እንዲካሄድ ዝግጅት አድርገዋል

83
ጥቅምት 2/2011 የዘንድሮ የመማር ማስተማር ሂደት ያለምንም ስጋት እንዲካሄድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ያነጋገርናቸው ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና የተማሪ ህብረት ፕሬዚዳንቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችን ገልጸዋል። በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተመስገን ጋሩማ እንደገለጹት መምህራን ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ትልቁን ሚና እንዲወጡ በተቋሙ እና በትምህርት ክፍላቸው እቅድ ላይ ውይይቶች እየተደረጉ ነው። ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የአንድነትና የሰላም ተምሳሌት እንዲሆኑ የቅድመ ውይይት ስራዎች እንደሚካሄዱና ከነቀምት ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመመካከር ብሄር ተኮር ስጋቶች እንዳይኖሩ ይደረጋል ብለዋል። መምህራን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አቋማቸውን በተማሪዎች ላይ ሳይጭኑ ገለልተኛ የሆነ ትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ አስተዳደራዊ ግዴታ አለባቸው፤ በአመለካከትም ይህንን እንዲያንፀባርቁ ይደረጋልም ብለዋል። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ ከተለያየ የሀገሪቱ አካባበቢ የሚመጡ ተማሪዎች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ገለጻና ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ተማሪዎች በመማር፣ መመራመርና መተግበር ቡድን በሚል አደረጃጀት ሀሳቦቻቸውን እንዲለዋወጡ በትምህርታቸው ላይ እንዲወያዩ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል። መምህራን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መልካም አርዓያ መሆን እንዳለባቸው የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ከመምህራን ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። ያልተገባ ድርጊት እንዳይፈፅሙ ክትትል እንደሚደረግና በሚያጠፉት ላይ ምክር ከመስጠት ጀምሮ እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርም ነው ያነሱት። የተማሪ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሲልኩ ትምህርታቸውን በሰላማዊ ሁኔታ እንደሚማሩላቸው እርግጠኛ መሆን አለባቸውም ብለዋል። ዶክተር ተመስገን በበኩላቸው ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ እንደ ቤታቸው የሚኖሩበትና የሚማሩበት ተቋም በመሆኑ የተማሪዎች የዕለት ከዕለት ሰላምና ፀጥታ የተጠበቀ እንዲሆን እንሰራለን ነው ያሉት። ተማሪዎች ያላቸውን የተለያየ ሀሳብ የማራመድ መብት ያላቸው ቢሆንም በእውቀትና በሰላማዊ ሁኔታ ማራመድ እንዳለባቸውም መክረዋል። የኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ጆሃር ሱልጣን ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖር የሰላምና ሌሎችን ክበባት በማሳተፍ ይሰራል ነው ያለው። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ የተለያየ የብሄር ማንነት ያላቸው ተማሪዎች የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን በውይይት የጋራ የሚያደርጉባቸው  መድረኮች እንደሚካሄዱ ነግሮናል። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ደሳለኝ ጌትነት ተማሪዎቹ በትምህርት ቆይታቸው እርስ በእርስ ተግባብተውና ተከባብረው ትምህርታቸውን እንዲማሩ  የሚያስችሉ ሥራዎች ይሰራሉ ነው  ያሉት። ዩኒቨርሲቲው ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ፣ ተማሪዎቹ ያላቸውን ጥያቄና ችግር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንሚገባቸው ተናግረዋል። ተማሪዎች በሚቆዩባቸው የትምህርት ዓመታት፣ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ብቁ ሆነው እንዲወጡ ዩኒቨርሲቲው በትጋት ይሰራል ብለዋል። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት አንተነህ ጥላሁን ተማሪዎች አንዳቸው ከሌላቸው እንዲተዋወቁ፣ የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያዳብሩ የማድረግ ስራ በህብረቱ እንደሚሰራ ነው የገለጸው። የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ህብረቱ ተገቢውን ክትትል እንዲሚያደርግና በስሩ የሚገኙ የተለያዩ ክበባትም ለዚህ ትክረት ሰጥተው እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያለው። በ2011 የትምህርት ዘመን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ 4 ሺህ 500፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከ6 ሺህ 800 በላይ፣ ደብረ መርቆስ ዩኒቨርሲቲ 4 ሺህ 720 ኣዲስ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ተዘጋጅተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም