በቀጣዮቹ አስር ቀናት አብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ ደረቃማ የአየር ሁኔታ ይኖራል

62
አዲስ አበባ  ጥቅምት  2/2/2011 በቀጣዮቹ አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ፣  ጸሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝንባቸው የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። በደቡብና በምዕራብ አጋማሽ ያሉ የአገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸውና እርጥበቱም ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ትንበያው አመልክቷል። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ደረቃማ የሆነው የአየር ጸባይ ዘግይተው ለተዘሩና እድገታቸውን ላልጨረሱ የመኸር ሰብሎችም ሆነ ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት አሉታዊ ተዕእኖ ይኖረዋል። በሌላ በኩል በደቡብና በምዕራብ አጋማሽ ያሉ የአገሪቱ አካባቢዎች የተሻለ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸውና እርጥበቱም ለግብርናው ዘርፍ አመቺ እንደሚሆን ትንበያው አመልክቷል። የሚገኘው ዝናብ ቀደም ብለው ለተዘሩ፣ ፍሬ በማፍራት ላይ ለሚገኙ፣ ዘግይተው ለተዘሩና በተለያያ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር የሚጠበቅ ይሆናል። እርጥበቱ በአርብቶ አደርና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውኃ አቅርቦት ጥሩ ጎን እንደሚኖረው ትንበያው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም