ኢትዮጵያ የቪዛ አሰጣጥ ስርዓቷን ለማሻሻል መወሰኗን የአፍሪካ ህብረት አደነቀ

1802

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2011 ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያን ቪዛ ስርዓት ለማሻሻል የወሰደችውን እርምጃ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ አደነቁ።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የስራ ዘመን መክፈቻ የጋራ ስብሰባ ወቅት ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ዜጎች ወደአገር ቤት የሚገቡበት አዲስ የቪዛ ስርዓት ለመዘርጋትና አፍሪካወያን ለማስተናገድ መወሰኗን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የሕብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂም ”ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን በመግለጽ፤ እርምጃው ሌሎች የሕብረቱ አባል አገሮች አፍሪካዊያን በአፍሪካ ውስጥ በነጻ እንዲዘዋወሩ የጀመሩትን ስራ የሚያበረታታ ነው” ብለውታል።

የአፍሪካዊያን ፓስፖርት ጉዳይ ስራ ያልጀመሩ ሌሎች አባል አገራትም እንዲገፉበት ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ ወርኃ ጥር ለሚደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ማኅበረሰብ ማቋቋሚያ ስምምነትም ሁሉም አባል አገሮች እንዲገኙና አፍሪካዊያን በአህጉራቸው ውስጥ በነጻ በሚዘዋወሩበትና ኑሮ በሚመሰርቱበት ጉዳይ ላይ ምክክር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

እስካሁን የአፍሪካ የነጻ ሰዎች እንቅስቃሴ ስምምነትን ከፈረሙ 32 አገሮች መካከል ሩዋንዳ ብቻ አጽድቃዋለች።

ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ 15 አገሮች ስምምነቱን እንዲያጸድቁት ይጠበቃል።

በአፍሪካ አህጉራችን ያለውን ነጻ የሕዝቦች እንቅስቃሴ እንዲጎለብት የአፍሪካ ህብረት በቀረፀው ፕሮግራም  ሁሉም የአፍሪካ አገሮች የመድረሻ ቪዛ እ.ኤ.አ እስከ 2023 እንዲሰጡ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የህብረቱ መቀመጫ የሆነችው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገሮች ዜጎች የመድረሻ ቪዛ መስጠት እንደምትጀምር ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸው ይታወሳል።

የቪዛ ስርዓቱን ማሻሻል ለኢኮኖሚ ትስስሩ አጋዥ ከመሆኑም ባለፈ የቱሪስት ፍሰት ለመጨመር በተለይም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት ማገዝ የሚያስችል እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የቪዛ ሥርዓቱ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶክተር ሙላቱ ”አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች የአለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቲከ ማዕከል በመሆኗ የምታስተናግዳቸው ኮንፈረንሶች ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመሩ ስለሚገኝ ለአፍሪካ አገራት ዜጎች የሚሰጠው የመዳረሻ ቪዛ ሥርዓትም ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ይሆናል” ሲሉ ባቀረቡት ሞሽን ላይ ተናግረዋል።