የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት በሃገር ውስጥና በውጭ መገናኛ ብዙሃን እይታ

63
የኢትዮጵያ ጣሊያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1880ዎቹ በተደረገ የሃገራቱ የትብብር ስምምነት ነበር። የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የትብብር ስምምነቶች እያደገና እየጎለበተ ዛሬ ላይ ደርሷል። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ የበለጠ ያጥናክረዋል የተባለ አጋጣሚም በዚህ ወቅት ተፈጥሮለታል። የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ለይፋዊ ጉብኝት ኢትዮዽያ ይገኛሉ። የህንንም አስመልክተው የተለያዩ የሃገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ዘገባዎቻቸውን እያሰራጩ ይገኛል። የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ ሲል ዘገባውን ቀድሞ ያሰራጨው ኢዜአ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደተቀበሏቸውም አስነብቧል። የአሜሪካው ፎክስ ኒውስ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀንድ እየመጣ ላለው መረጋጋት ምሰሶ ናት ሲሉ ማድነቃቸውን ፅፏል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ ሰላም ስምምነቱ ከመጡ በኋላ የመጀመሪያው ምዕራባዊ መሪ መሆናቸውን የዘገበው የዜና ምንጩ በዛሬው ዕለትም ወደ ኤርትራ በማቅናት ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እንደሚገናኙም ጥቆማ ሰጥቷል። የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጉብኝት ከህገወጥ ስደት ጋር የተያያዘ አጀንዳ ሊነሳበት እንደሚችል በዘገባው ያስነበበው ደግሞ አር ኤፍ አይ ድረ ገፅ ነው። ድረ ገፁ የቀድሞ የጣሊያን የምክር ቤት አባል የሆኑትን ኒኮላ ላቶሬን ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያን ብሎም የመላው አፍሪካን ግንኙነት ለማሳደግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት እጅግ አስፈላጊው ጉብኝት እንደሆነም ጠቅሷል። ከአፍሪካ ወደ ጣሊይን የሚደረገው ፍልሰት መጠኑ ቢቀንስም አሁንም የጣሊያን ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እንደቀጠለም አር ኤፍ አይ አክሏል። ኢትዮጵያና ጣሊያን በኢኮኖሚ ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፍ ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ መናገራቸውን በመጥቀስ የዘገበው ፋና ብሮድካስቲንግ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ በብሄራዊ ቤተመንግስት ክብራቸውን የሚመጥን የእራት ግብዣ እንደተደረገላቸውም ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጦችን ማድነቃቸውንና ለለውጡ እንቅስቃሴ ሃገራቸው ድጋፍ እንደምትቸረው መናገራቸውን ፋና አንስቷል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የደረሱትን የሰላም ስምምነት ለመደገፍ ያለመ ጉብኝት የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እያደረጉ መሆናቸውን የዘገበው ኒውስ 24 ህገወጥ ፍልሰትና በፈጣን የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ባስመዘገበችዋ ሃገር የሚኖሩ የኢንቨስትመንት ጉዳዮች በጉብኝቱ ሂደት የሚነሱ ጉዳዮች እንደሆኑም መረጃውን አሰራጭቷል። የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ እያደረጉ ያለውን ጉብኝት እንዳጠናቀቁ ወደ ኤርትራ እንደሚያቀኑም ኒውስ 24 በዘገባው አካቷል። ሜይል ኦንላይን በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ኢትዮጵያን ‘’የአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ምሰሶ’’ በማለት ማሞካሸታቸውን በማስቀደም  ዘገባውን ይዞ ወጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ በጋራ የሰጡትን መግለጫን ተንተርሶ ሜይል ኦንላይን ሁለቱ ሃገራት በኢንቨስትመንት፣ በንግድና መሰረተ ልማት እንዲሁም በፍልሰት ረገድ ተባብረው ለመስራት ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሷል። ኢዜአ በተያያዘ ዘገባው ጣሊያን በኢትዮጵያ የከተሞች የውህና ፍሳሽ አገልግሎትን ለማሻሻል የሚውል የ696 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጓን አንስቷል። እንደ ዘገባውም 158 ሚሊዮን ብሩ በቀጥታ ድጋፍ መልክ እንዲሁም ቀሪው 538 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ በረጅም ጊዜ በሚከፈል ብድር ጣሊያን ድጋፍ አድርጋለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለበርካታ አመታት በመሃከላቸው የነበረውን ቁርሾ አስወግደው ወደ ሰላም ስምምነት መምጣታቸውን በሳል እርምጃ ሲሉ ማድነቃቸውን ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በፌስቡክ ገፁ ያሰራጨው መረጃ አመልክቷል። የሰላም ሂደቱ ከሁለቱ ሃገራት አልፎ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት አዲስ በር የከፈተ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ዋቢ ያደረገው መረጃው አክሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ የኢትዮጵያ ቆይታቸውን በመቀጠል የዛሬ 40 አመት በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግስት የህብረት ሽርክና የተቋቋመውን አምቼ ሲ ኤን ኤች የተሰኘውን የጣሊያን ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጐብኝተዋል። ኩባንያው የጭነት እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ላለፉት አራት አስርተ አመታት እየገጣጠመ ለሃገር ውስጥ ገበያ ሲያቀርብ የቆየ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለውን ጉብኝት በማጠናቀቅ ወደ ኤርትራ እንደሚያመሩና በዚያውም የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን እንደሚያገኙም የሃገር ውስጥም ሆኑ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ተቀባብለው እየዘገቡት ይገኛሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም