ኢትዮጵያ እያመጣችው ላለው አገራዊና ቀጠናዊ ለውጦች ላይ ጣሊያን አብራ ትሰራለች

66
አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2011 ኢትዮጵያ እያመጣችው ባለው አገራዊና ቀጠናዊ ለውጦች ላይ ጣሊያን አብራ እንደምትሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ገለጹ። በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጁሴፔ ኮንቴ ኢትዮጵያ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ እያመጣችው ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ አድንቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ትናንት የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል። በስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የነበራትን የረዥም ጊዜ ቅራኔ ባጭር ጊዜ መፍታቷ የሚደነቅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካን ሲጎበኙ ጉብኝታቸውን ከኢትዮጵያ በመጀመራቸው ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረው፤ በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካና ሰላም መረጋጋት ላይ ከኢትዮጵያ ጋር አብረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል። ጣሊያን የኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር መሆኗንና አሁን ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ሁለቱንም አገሮች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ለማጠናከር ዝግጁ መሆናቸውንም አብራርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላለፉት ወራት በአገር ውስጥና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የፖለቲካ ምህዳር ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጓን ገልፀውላቸዋል። በተለይም በአገር ውስጥ የነበረውን የህዝብ ጥያቄ ከመመለስና አገሪቱ ወደ ትክክለኛው መስመር እንድትገባ ከማድረግ፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የነበራትን የሰላም ማስከበርና የአስታራቂነት ሚና ከፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ለውጥ መመዝገቡንም እንዲሁ። ከነዚህም መካከል ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው የሰላም ስምምነትና አብሮ የመስራት ሁኔታ፣ የደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲመለስ የተደረገው የማስማማት ሂደት ተጠቃሽ መሆናቸውንም ገልፀዋል። "መንግስታችን በሰላም፣ አብሮ በመስራትና በኢኮኖሚ ትስስር የሚያምን ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጣሊያንና ኢትዮጵያ አሁን እየመጣ ባለው ቀጠናዊና አገራዊ ምቹ ሁኔታዎች ላይ በትብብር መስራታቸው የሁለቱንም አገሮች ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑንም ገልፀዋል። ጣሊያንና ኢትዮጵያ ታሪካዊና የቆየ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውንና በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማሳደግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውንም ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም