ህገ ወጥ የመንገድ ዳር ንግድ ለኪሳራ እየዳረገን ነው —የሐረር ከተማ ህጋዊ ነጋዴዎች

1087

ሐረር ጥቅምት 1/2011 ህገ- ወጥ የመንገድ ዳር ንግድ መበራከት ለኪሳራ እየዳረገን ነው ሲሉ በሐረር ከተማ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ንግድ ሥራ የተሰማሩ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን ገለፁ።

የክልሉ ንግድ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራሁ ነው ብሏል ።

በከተማው በተለምዶ ስላሴ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ንግድ ስራ የተሰማሩ አቶ መኮንን ሐምዛ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ህገ ወጥ የመንገድ ዳር ላይ ንግድ መበራከት ለኪሳራ እየዳረጋቸው ነው።

“በመንገድ ዳር በተመሳሳይ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች ምርቶቹን በዝቅተኛ ዋጋ ለገበያ ስለሚያቀርቡ የቤት ኪራይና ግብር የምንከፍለውን ህጋዊ ነጋዴዎች ገበያ በማሳጣት ለኪሳራ እየተዳረግን ነው” ብለዋል።

” የክልሉ መንግስት ህገ- ወጦችን ወደ ህጋዊነት አንዲያስገባ ጠይቀዋል ”

በህጻናት አልባሳት ንግድ ስራ የተሰማራው ወጣት ሱራፌል ሲሳይ በበኩሉ “የጎዳና ላይ ህገ-ወጥ ንግድ መበራከት ለምርታችን ገበያ እያሳጣን ነው” ብሏል ።

“በተመሳሳይ ምርት የሚካሄድ የጎዳና ላይ  ህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት ህጋዊዎችን ከገበያ እያሶጣንና ለኪሳራ እየዳረገን ነው ” ብሏል።

የክልሉ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ነጋዴዎቹ ጠይቀዋል ።

በሐረር ከተማ በተለምዶ ሲጋራ ተራ ተብሎ በሚጠራው የገበያ ቦታ በጎዳና ላይ ንግድ የተሰማራው ወጣት ተክሌ ጥላሁን በበኩሉ ለተሰማራበት የአልባሳት ንግድ ሥራ በከተማው ልዩ ስሙ “ደከር” በተባለው አካባቢ መነገጃ ቦታ እንደተሰጠው ገልጿል።

” ከሁለት ዓመት በፊት ቦታው ቢሰጠንም ገበያ የሌለው በመሆኑ ገዥ ወደምናገኝበት ቦታ ተዘዋውረን ለመሸጥ ተገደናል” ብሏል

በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ቁጥጥርና ጥበቃ ዲቭዥን ኃላፊ ኮማንደር ሙኒብ አብዱልፈታህ በበኩላቸው በከተማው በተለምዶ አራተኛ፣ ሲጋራ ተራና ሸዋበር በሚባሉ አካባቢዎች ህገ ወጥ የመንገድ ላይ ግብይት ተበራክቷል።

የጎዳና ንግዱ ለትራፊክ እንቅስቃሴ መጨናነቅ አስተዋጽኦ እያደረገና ለአደጋ መንስኤ እየሆነ መጣቱን ኮማንደር ሙኒብ ጠቁመዋል።

የክልሉ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብደላ መሐመድ በበኩላቸው “በከተማው በመንገድ ዳር የሚከናወን ህገ ወጥ ንግድን ለማስቀረት ጥረት ቢደረግም ሙሉ ለሙሉ መፍትሄ ማምጣት አልተቻለም ” ብለዋል ።

“ችግሩ በአንድ አካል የሚፈታ ሳይሆን የተለያዩ ባለድርሻ አላትን ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ በሙሉ አቅም ወደ ስራ መግባት አልተቻለም” ብለዋል።

“ከዚህ ቀደም በተለምዶ ደከር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 300 የሚሆኑ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ህጋዊ  የማድረግ ስራ ቢከናወንም አሁንም ችግሩ ቀጥሏል” ያሉት ደግሞ በክልሉ ንግድ ጽህፈት ቤት የፍትሃዊ ንግድ ግብይት ልማት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ መሀመድ ዩስፍ ናቸው ።

ህገወጥ የመንገድ ዳር ንግድ እንዲስፋፋ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ በአካባቢው ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋትን ተከትሎ ደንብ የማስከበር ሥራው መላላት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ደንብ አስከባሪን ጨምሮ የህግ የበላይነትን የሚያስከብር አካል አለመኖርና በቅንጅት አለመንቀሳቀስ ሌላው ምክንያት መሆኑንም አቶ መሀመድ የተናገሩት።

ጽህፈት ቤቱ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት በአሁኑ ወቅት ከክልሉ የጸጥታ አካላት፣ ማዘጋጃ ቤትና ከከተማ ልማት ጋር በመቀናጀት ወደ ስራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑን አቶ መሀመድ አስታውቀዋል ።