ዓለም የቱሪዝም ቀን በደቡብ ክልል በሆሳዕና ከተማ ተከበረ

1357

ሆሳእና ጥቅምት 1/2011 የቱሪስት መዳረሻዎችን በአግባቡ በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በደቡብ ክልል ደረጃ ለ24ተኛ ጊዜ በሆሳዕና ከተማ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አክመል መሀመድ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ቱሪዝም ለሀገሪቱ እድገትና ልማት የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ሀገሪቱ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች መገኛ ብትሆንም ሃብቱን አልምቶና ጠብቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የቱሪስት መዳረሻዎችን በአግባቡ በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች ለውጦች ቢኖሩም የጎብኚዎች ቁጥር አሁንም በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ነው የገለጹት፡፡

” በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በቅንጅት መስራት አለብን ” ብለዋል፡፡

የደኢህዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው የቱሪዝም መዳረሻዎች በአግባቡ አለመልማታቸው ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡

“የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ ጀምሮ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በዘርፉ በተመረቁ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

ከበዓሉ ተሳታፊዎቹ መካከል የሀላባ ልዩ ወረዳ ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ መሀመድኑር ሌራሞ እንዳሉት በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የቱሪዝም ዘርፉን በዕቅድ መምራት ያስፈልጋል።

“ዘመናዊና ዲጂታል አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት ሀብቶችን በአግባቡ በመጠበቅና በማልማት ሀገሪቱን በዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግና ይኖርብናል” ብለዋል፡፡

“በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከማህበረሰቡና ከባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ መስራት ይገባል” ያሉት ደግሞ በሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝምና መስህብ ሥፍራዎች ጥበቃና ልማት ግብይት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ጎበና ጎዳና ናችው፡፡

ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አገልግሎቱን ወደ ዲጂታል መለወጥ፣ የጎብኚዎችን ፍላጎት ከዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ጋር ማስተሳሰር፣ የአየር ትራንስፖርቱን ይበልጥ ምቹ ማድረግ የሚሉትን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሄዎች በመድረኩ ተንጸባርቀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች ከፓናል ውይይቱ በተጨማሪ በሃድያ ዞን የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።