የጤና ባለሙያዎችን እጥረትና የአቅም ውስንነት ለማቃለል እየተሰራ ነው-የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

959

ባህር ዳር ጥቅምት 1/2011 በድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ጨምሮ በጤናው ዘርፍ የባለሙያዎችን እጥረትና የአቅም ውስንነት ለማቃለል ለስልጠናና አቅም ግንባታ ትኩረት መስጠቱን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በ2010 በጀት አመት የስራ አፈጻጸምና በ2011 ዕቅድ አቅጣጫ ላይ በክልሉ ከተውጣጡ የጤናው ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በባህር ዳር እየተወያየ ነው።

የቢሮው የሕክምና አገልግሎት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አበበ ዳኛው ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉን ካለው የህዝብ ቁጥር አኳያ በቂ የጤና ተቋማት ካለመኖራቸው በተጨማሪ በዘርፉ ያለው የባለሙያ እጥረትና የአቅም ውስንነት በሕክምና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተግዳሮት ሆኗል።

በክልሉ ውስጥ ካሉ 840 ጤና ጣቢዎች ውስጥ በ60 ዎቹ በልዩ ሁኔታ የአስቸኳ ቀዶ ህክምና ለማካሄድ ታስቦ በቁሳቁስና በመሳሪያ እንዲደራጁ ቢደረግም በባለሙያ እጥረት አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

“ከክልሉ ህዝብ ቁጥር አኳያ ከ210 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ቢያስፈልጉም በስራ ላይ ያሉት 68 ብቻ ናቸው ” ብለዋል ።

ባሉት ሆስፒታሎች ቁጥር ልክ የሚፈለገውን የባለሙያዎች መጠን ሟማላት ካለመቻሉ በተጨማሪ በስራ ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ ባለሙያዎች በትምህርት ደረጃቸው በዲፕሎማ ደረጃ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

“በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን ሳይጨምር ካሉት ከ 47 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች ውስጥ ከ 50 በመቶ በላዮቹ በተመደቡበት ሙያ የአቅም ውስንነት አላቸው ” ሲሉም ተናግረዋል ።

እንደ አቶ አበበ ገለጻ የቤተ-ሙከራ፣ የራጅና ሰመመን ሰጪ ባለሙያዎች እጥረት ደግሞ በሕክምና አሰጣጡ ዋነኛ ተግዳሮት ነው ።

ቢሮው በጤና ተቋማት ያለውን የባለሙያዎች እጥረትና የአቅም ውስንነት ለማቃለል ለስልጠናና አቅም ግንባታ ትኩረት መስጠቱን አስተባባሪው ተናግረዋል ።

በክልሉ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎችና የጤና ሳይንስ ኮሌጆች ጋር በመተባበር በዚህ ዓመት በሰራ ላይ ላሉ 120 ባለሙያዎች በልዩ የህክምና ዘርፍ (ስፔሻሊስት) ስልጠና ለመስጠት ምልመላ መካሄዱን ለአብነት ጠቀሰዋል ።

ከስፔሻሊስት ሃኪሞች በተጨማሪ የባለሙያዎችን የትምሀርት ደረጃ  በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ የማሳደግና በአዋላጅ ነርሰነት ስልጠና የመስጠት ስራዎች በስፋት እንደሚከናወኑ አስተባባሪው አስታውቀዋል ።