አረጋዊያን ከልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረግ ይገባል----የኦሮሚያ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ

90
አዳማ ጥቅምት 1/2011 አረጋዊያን በክልሉ እየተከናወነ ካለው ሁሉን አቀፍ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የኦሮሚያ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ። "ቀደምት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆኑ አረጋዊያንን ተሳታፊና ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን"  በሚል መሪ ቃል የአረጋዊያን ቀን በክልል ደረጃ በአዳማ ከተማ ተከብሯል። የኦሮሚያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲያ ሙሀመድ እንደገለጹት የአረጋዊያንን ቀን በየዓመቱ ጠብቆ መዘከር ብቻ ሳይሆን እየተከናወነ ካለው ሁሉን አቀፍ ልማት በየደረጃው ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል። "አረጋዊያን ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ አሻራ ያሰረፉ የአገር ባለውለታ ናቸው" ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ  አቅምና ጧሪ በማጣት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን አረጋዊያን ከልማቱና ከዕድገቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አሰራር ተዘርግቶ ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል። ሙያዊ እውቀትና አቅም ያላቸው አረጋዊያን በሙያቸው ተደራጅተው እንዲሰሩና ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የመስሪያና የመሸጫ  ህንጻ መገንባት የሚችሉበት ቦታ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አዳማ፣ አምቦ፣ ዝዋይ፣ ሻሻመኔ ከተሞችን ጨምሮ በለገጣፎና አዳሚ ቱሉ ወረዳ የአረጋዊያንን ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል አበረታች ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ወይዘሮ ፈቲያ ተናግረዋል፡፡ " ወጣቱ ትውልድ አረጋዊያንን በጉልበቱ፣ በእውቀቱና በገንዝቡ ጭምር በመደገፍና በመንከባከብ የመኖር ተስፋቸው እንዲለመልም ማድረግ ይኖርበታል" ሲሉም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ አረጋዊያን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተፈራ ኤዳኤ በበኩላቸው " አረጋዊያን የአገር ሉዓላዊነት፣ የህዝቦች ባህልና ታሪክ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍ ያደረጉ ጀግኖች ከመሆናቸውም ባሻገር በአገር ፍቅርና እንድነት መጠናከር ላይ የሰሩ ናቸው " ብለዋል፡፡ በክልሉ በሚከናወኑ ልማቶች አረጋዊያን ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማህበሩ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ሊቀመንበሩ አቅምና እውቀት ያላቸው አረጋዊያን በሙያቸው እንዲደራጁ መደረጉን ተናግረዋል። "አቅም የሌላቸውና ድጋፍ ያጡ አረጋዊያን የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ መንግስት አሰራር ዘርግቶ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ነው" ብለዋል፡፡ የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ እንድሪስ በበኩላቸው የከተማው አስተዳደር ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ አረጋዊያንን የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ በማድረግ የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ መደረጉን አስረድተዋል። የአረጋዊያን ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ  ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ለሁለገብ የገበያ ማዕከል ግንባታ የሚውል ከ6 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ቦታ ለከተማዋ አረጋዊያን ማህበር መሰጠቱንም ገልጸዋል። በአዳማ ከተማ ዛሬ በተከበረው ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከ250 በላይ አረጋዊያን የብርድ ልብስ እርዳታ እንዲያገኙ ተደርጓል። በበዓሉ ላይ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች የተወጣጡ የአረጋዊያን ማህበር አመራሮችና አባላትን ጨምሮ የክልሉ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም