አጋር ድርጅቶች በኢህአዴግ ምክር ቤት መወከላቸው ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚያግዛቸው ተናገሩ

1604

አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች ውስጥ የሚያከናውኑት ተግባራት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸው የአጋር ድርጅቶች አመራር አባላት ገለፁ።

አጋር ድርጅቶቹ በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፉ መወሰኑ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ነው የጋምቤላ፣ የሶማሌና የአፋር ክልላዊ መንግስታት አመራር አባላት ያመለከቱት።

የሱማሌ ዴሞራሲያዊ ፓርቲ (ሱህዴፓ)፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ)፣ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሀብሊ) እና የጋምቤላ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን) ለረጅም ዓመታት የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ሆነው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

በሥም የሚጠሩባቸውን ክልሎች በመምራት ላይ የሚገኙት ድርጅቱ  የኢህአዴግ አባል ድርጅት ለመሆን ተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም ምላሽ ባለማግኘቱ ቅሬታ እንደነበረባቸው ተናግረዋል።

ኢህአዴግ ሰሞኑን ባካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤው ግን እነዚህ ድርጅቶች አጋርነታቸው አድጎ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በግንባሩ ምክር ቤት እንዲወከሉ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሰረት የአጋር ድርጅቶቹ ያለ ድምጽ አስተያየትና ገንቢ ሐሳቦችን በመስጠት ልምድ እንዲወስዱ ይደረጋል።

በቀጣይም ሙሉ በሙሉ የድርጅቱ አባል የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥናት እንደሚካሄድ በጉባዔው ላይ ተገልጿል።

ድርጅቶቹ በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ መወከላቸው በሚመሯቸው ክልሎች ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲገኝ ለማስቻል የሚያግዝ አቅም እንደሚፈጥር ነው የአመራር አካላቱ የተናገሩት።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጋትሉዋክ ቱት እንደሚሉት እነዚህ ክልሎች ሁለንተናዊ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከቱ ውሳኔዎች ላይ የነበራቸው ተሳትፎ አናሳ ነው፤ ምክንያቱም “በህግ ከተቋቋሙት 9 ክልሎች መካከል አብዛኛው  አገራዊ ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉት አራት ክልሎች ብቻ ናቸው” ብለዋል።

ይህ ደግሞ “ታዳጊ ክልሎች ላይ ቅሬታ ሲያስነሳ ነበር” ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ።

የኢህአዴግ የአሁኑ ውሳኔ ግን ለዓመታት ሲነሳ የቆየውን የነበረው ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

በ11ኛው የድርጅቱ ጉባዔ አጋር ድርጅቶቹ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ መወሰኑ ክልሎቹ  ከድጋፍ ባለፈ ራሳቸውን ችለው በአገር ልማት ላይ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ የሚረዳ መሆኑንም ይናገራሉ።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሃጂ ስዩም አወል በበኩላቸው አራቱ መሪ ድርጅቶች ውሳኔ ወስነው ከጨረሱ በኋላ ለአጋር ድርጅቶች ማሳወቃቸው ተገቢ አልነበረም ይላሉ።

ድርጅቱ  አጋር ሳይሆን አባል ለመሆን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቢያነሱም ምላሽ ሳያገኝ መቆየቱን  አስታውሰዋል።

አጋር ድርጅቶቹ እኩል ዕድል ከተሰጣቸው ለአገሪቷ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም ሃጂ ስዩም ያነሳሉ።

የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ መሐሙድም እንደ ጋምቤላና አፋር ክልሎች የሱማሌ  ክልል ህዝቦችም ድርጅቶቹ ቀጥተኛ ተሳታፊ ባለመሆናቸው ቅሬታ አድሮባቸው እንደነበር ነው የተናገሩት።

ክልሉ በዚሁ ጉዳይ ተደጋጋሚ ጥያቄ አንስቶ የነበረ ቢሆንም እስከ ኢህአዴግ 11ኛ ጉባዔ ምላሽ አለማግኘቱንም አስታውሰዋል።

ውሳኔው  ሁሉም ክልሎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ  በመሆን አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም አቶ ሙስጠፋ አመልክተዋል።