ኢትዮጵያና ቱኒዚያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ይሰራሉ

1830

አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 ኢትዮጵያና ቱኒዚያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር  አክሊሉ ኃይለሚካኤል በቱኒዚያ የውጪ ንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ሂቻም ቤን አህመድ የተመራ የቢዝነስ ልዑክን ቡድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱ የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር  አክሊሉ ኃይለሚካኤል፤ ”ውይይቱ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ ዘይት ከቱኒዚያ እንደምታስገባ የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው አሁን ግን የቱኒዚያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰሳቸው አገሪቱ የውጪ ምንዛሬ እንድታድን ማስቻሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ቱኒያዚያ በትምህርት፣ ቱሪዝም እና ኢንዱስትሪ ልማት ያላትን ልምድ የመቅሰም ፍላጎት እንዳላትም ገልፀዋል።

የቱኒዚያ የውጪ ንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ሂቻም ቤን አህመድ በበኩላቸው፤ ቱኒዚያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትሻ አስታውቀዋል።

ሁለቱ አገሮች ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነት ቢኖራቸውም በንግድ በኩል ያላቸው ግንኙነት  ዝቅተኛ መሆኑን አክለው ጠቅሰዋል።

የሁለቱ አገሮች አጠቃላይ ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ መጠን ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ነው።