የምሽት ዝርፊያና ንጥቂያን ለማስቀረት ሕግን በአግባቡ መተግበር ይገባል- በአርባምንጭ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

73
አርባምንጭ ጥቅምት 1/2011 በአርባ ምንጭ ከተማ በምሽት የሚፈፀም ዝርፊያና ንጥቂያን ለማስቀረት ሕግን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ። የከተማው ፍትህ፣ ጸጥታና ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት በበኩሉ "ወንጀሉን በጋራ ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል" ብሏል። በከተማው የቤሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መስፍን ስለሽ ለኢዜአ እንደገለፁት በከተማው በምሽት የሚፈፀም የተንቀሳቃሽ  ስልክ ንጥቂያ እየተበራከተ መጥቷል ። "ድርጊቱ ከዚህ በፊት አልፎ አልፎ የሚስተዋል ቢሆንም አሁን ላይ በተደራጀ መንገድ በተሽከርካሪ ታግዞ መፈፀሙ በነዋሪው ዘንድ አሳሳቢ ሆኗል" ብለዋል ። በድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይ ጥብቅ ርምጃ በመውሰድ ወንጀሉን ለማስቀረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ መስፍን ጠቁመዋል። በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የ2ኛ ዓመት የማናጅመንት ተማሪ እንግዳው እዮብ በበኩሉ በቅርቡ ዘረፋ ተፈፅሞበት ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን አስታውሷል፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ የደብተር መያዣ ቦርሳና ለቀለብ የያዘውን መጠነኛ ገንዘብ መነጠቁን የገለፀው ተማሪው ሌሎች ተማሪዎችም ተመሳሳይ ወንጀል እንደተፈፀመባቸው ተናግሯል ። የአባያ ክፍለ ከተማ ነዋሪና የህግ ባለሙያ አቶ ኃይለሚካኤል ጉላንት "ለወንጀል መስፋፋት ምክንያቱ የህግ መላላት ሲሆን መፍትሄውም ህጉን በአግባቡ መተግበር ነው " ብለዋል ። ፖሊስ ብቻውን ወንጄል መከላከል እንደማይችል የገለጹት አቶ ኃይለሚካኤል "ህብረተሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ይዞ ራሱንና አከባቢውን ከወንጀል እንዲከላከል ከማብቃት ጀምሮ ጸጥታ አካላት ተቀናጅተው መስራት አለባቸው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ። የአርባምንጭ ከተማ ፍትህ፣ ፀጥታና ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ፃራ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የወንጀል ድርጊቱ መኖሩ ተደርሶበት እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል። ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ በድርጊቱ በቀጥታ የተሠማሩ 28 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ፖሊስ እየተጣራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ። በወንጀሉ የተጠረጠሩና ሰሌዳ የሌላቸው 123 ባለ ሦስት እግር ባጃጆችና 78 ባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶችም በቁጥጥር ስር ውለው በአሽከርካሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። "የወንጀል ድርጊቱን በዋናነት የሚያስተባብሩ እንዲሁም ስምሪትና ከለላ የሚሰጡ አካላትም  ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ነው" ብለዋል ። ህብረተሰቡ በድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን አሳልፎ ለህግ በመስጠት ወንጀሉን የመከላከል ስራ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም