በኢትዮጵያ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በሳይንስና ምርምር እንደሚደግፉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ገለፁ

78
አዲስ አበባ ጥቅምት1/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በሳይንስና ምርምር እንደሚደግፉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ገለፁ። የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዝዳንቶች የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ሰሞኑን 11ኛ ጉባኤው ላይ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች  ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ መሆናቸውን አክለዋል። ኢህአዴግ በጉባኤው በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ያስችላሉ ያላቸውን የተለያዩ አቅጣጫዎች ይፋ አድርጓል። ለአቅጣጫዎቹ ገቢራዊ መሆን ደግሞ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ድጋፍ የጠየቀ ሲሆን፤  ይህ ጥሪ ከቀረበላቸው አካላት መካከል ምሁራን ዋነኞቹ ናቸው። ኢዜአ  በጉዳዩ ዙሪያ የዋቸሞ፣ የጅማና የአዲስ አበባ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችን አነጋግሯል። ፕሬዝዳንቶቹ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ለውጥ ፍሬያማ እንዲሆንና ቀጣይነት እንዲኖረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛ የማይተካ ሚና አለው። የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጣሰው ገብሬ በለውጡ ዙሪያ በሚገጥሙ ችግሮች ላይ  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙያዊና ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን ማበርከት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ በፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ለውጡ ቀጣይነት የሚኖረው ተቋማዊ ሲሆን ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢህአዴግ በ11ኛ ጉባኤው ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ እንደሚሰራ መግለጹን ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን አውስተዋል። የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለውጡን ወደ ፊት ለማራመድ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ በተለይ 'ልዩነቶች ምክንያታዊ በሆነ አግባብ እንዴት ይፈታሉ' የሚለው ሃሳብ ላይ ጥናት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የህግ የበላይነት አለመከበር እና ስራ አጥነት የአገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረው፤ ገዢው ፓርቲ ባካሄደው ጉባኤ በእነዚህ ችግሮች ላይ ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጡን አድንቀዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምር ከመስራት ባሻገር የምርምር ውጤቶችን ገቢራዊ በማድረግ ለአገራቸው ሁለንተናዊ ለውጥ የድርሻቸውን ይወጣሉ የሚል እምነት እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኑርልኝ ተፈራ ናቸው። በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ መሰረት እንዲይዝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ጉልህ እንደሆነ ገልጸው፤ ኢህአዴግ በጉባኤው የተቋማቱን አገራዊ ፋይዳ የሚያጎለብት ሪፎርም ተግባራዊ እንደሚደረግ አቅጣጫ ማስቀመጡን "ወቅታዊ ውሳኔ" ሲሉ ገልጸውታል። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋምት ከመቸውም ጊዜ በላይ ችግር ፈች ጥናቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ከዚህ ስራ ጋር በሚጣጣም መልኩ እንደሚደራጅም ተናግረዋል። የምሁራንና የምርምር ማእከላት የሆኑት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  ዴሞክራሲን፣ ሰላምንና ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አቅጣጫዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም