በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የድርሻችንን እንሰራለን-የትህዴን አባላት

62
መቀሌ ጥቅምት1/2011 የተጀመረውን ለውጥ በሰላማዊ የትግል ሂደት ለማስቀጠል ከመንግስትና ከህዝባችን ጎን ተሰልፈን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትህዴን አባላት ገለጹ። የንቅናቄው አባላት ትናንት በሁለት አቅጣጫዎች ከቆየበት የኤርትራ መሬት ወደ ትግራይ የገቡ ሲሆን፣አንድ ሺህ 150 ያህሉ በዛላንበሳ በኩል ውቅሮ ከተማ ሲገቡ ሌሎች አንድ ሺህ 150 ያህሉ ደግሞ በትግራይ ማእከላዊ ዞን ዓብዪ ዓዲ ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በውቅሮ ከተማ ትናንት ማምሻውን ከገቡት የንቅናቄው አባላት መካከል አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው አዲስ ለውጥ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ ትውልድ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል። ከንቅናቄው ጋር ተሰልፎ ላለፉት 16 ዓመታት ሲታገል የቆየውና ትናንት የተመለሰው ደጀን ተክለተስፋይ እንደገለጸው የትጥቅ ትግል ማካሄድ እጅግ መራራና ውጣ ውረድ የበዛበት ነው። ለህዝቦች የፍትህ ጥያቄ ሲል ለረጅም ዓመታት ሲታገል መቆየቱን ገልጾ አሁን በተፈጠረው የሰላም አማራጭ ተጠቅሞ ትግሉን ለማስቀጠል መዘጋጀቱን ተናግሯል። ከንቅናቄው ጋር በመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የቆየው ወጣት ጸሃይ አርአያ በበኩሉ፣የኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በተፈጠረው የለውጥ ጉዞ ያለምንም ስጋት ወደ ትውልድ ሃገሩ ሊመለስ መቻሉን ተናግሯል። ለትጥቅ ትግል ካበቁት አያሌ ምክንያቶች መካከል አንዱ የስራ እድል ማጣት መሆኑን ገልጾ ሁኔታዎች ተመቻችተው እድሉን ሲያገኝ የጀመረውን ሰላማዊ የትግል መስመር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል። ለ15 ዓመታት ስትታገል የቆየችውና ከሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የንቅናቄው ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የሆነችው ዛይድንጉስ ተስፋይ እንዳለችው በትጥቅ ትግል ቆይታዋ ብዙ ውጣ ውረዶችና ስቃይ አይታለች። ዛሬ ያንን መከራ አልፋ ወደ ትውልድ ሃገሯ በሰላም መመለሷ ልዩ ደስታ እንደፈጠረባት ገልጻ በሰላማዊ ትግል የቀሩ የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እንደምትሰራም ጠቁማለች። ሌላው ተመላሽ ወጣት ኤፍሬም ሕሉፍ ደግሞ የማታገያ መንገዶች በመዘጋታቸው የመጨረሻ ብቸኛው አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል ላለፉት 15 ዓመታት ማካሔዱን ገልጿል። አሁን የተፈጠረውን የለውጥ ሁኔታ በመጠቀም ከህዝቡ ጋር በመሆን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ እንደሚታገልም አስረድቷል። አባላቱ የትግራይ ክልል ህዝብ በተለይም የዛላንበሳና የውቅሮ ከተማ ነዋሪዎች በየመንገዱ ለረጅም ሰዓታት ቆመው ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል። የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሃገራቸው ከገቡ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ኤርትራ ውስጥ ለ17 ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አንዱ ነው። የንቅናቄው አባላት ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀር፣በህገ-መንግስት ጽንሰ ሃሳብና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ለማወቅ ተችሏዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም