ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማንና የፓርቲዎችን ዓርማ አደባልቆ መገንዘብና መመልከት ተገቢ አይደለም

83
አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማና የፓርቲዎችን አርማ በማደበላለቅ የተዛባ አመለካከት መያዝ አግባብነት የለውም ሲሉ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ገለጹ። የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች የ11ኛው ሰንደቅ ዓላማ ቀን ''ሰንደቅ ዓላማችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችን'' በሚል መሪ ሐሳብ በውይይት አክብረዋል። የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ሰንደቅ ዓላማን አስመልክተው ያለውን አለም አቀፍ ተሞክሮና የአገራችንን የሰንደቅ አላማ አጀማመርና አጠቃቀም ታሪክን በተመለከተ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል። በዚህም አብዛኛው የዓለም አገራት ብሄራዊ ዓርማቸው በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ እንደተገለጸና በተመሳሳይም የአገራችን ሰንደቅ ዓላማም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ መሆኑን በመነሻ ፅሑፉ ላይ ተገልጿል። የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ አስመልክቶ ጥያቄ የሚያነሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ዴሞክራሲያዊ በሆነና የተጀመረውን ለውጥ በሚያስቀጥል መልኩ በአገሪቱ ህዝብ ከታመነበት ሊሻሻል እንደሚችል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል። ነገር ግን በሥራ ላይ ያለውና በህገ መንግሥቱ አንቀጽ ሶስት የተደነገገውን ማክበር እንደሚገባም ለተወያዮቹ ሃሳብ ቀርቧል። የበዓሉ ተሳታፊዎች እንዳነሱትም የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበና የህዝቦችና ሃይማኖቶች እኩልነት እንዲሁም መቻቻልና መተማማን የሚፈጥር ሰንደቅ ዓላማ ሊኖረን ይገባል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በአገራችን በፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል የአንዱን አርማ በአንዱ ላይ የመጫን ፍላጎት እንዲሁም የፓርቲዎችና ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ የማደበላለቅ የተዛባ ግንዛቤና አመለካከት ይታያል ይህን ጉዳይ ለማስተካከልም መንግስት መስራት አለበት ብለዋል። "አንድን ብሄር ወይም የህብረተሰብ ክፍል የሚወክል ሰንደቅ ዓላማ ሊኖር አይችልም፤ አንዱ ብሄር ላይ የራስህን ትተህ የእኔን ተቀበል ብሎ የሚጫንበት ሰንደቅ ዓላማም ሊኖር አይችልም" ያሉት ደግሞ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ናቸው። በመሆኑም ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን በህዝቦች መቻቻል ፤መፈቃቀድና፣መፈቃቀር፣ አብሮ መኖር ላይ የተመሰረተና የማንነትና ሃይማኖቶች እኩልነትና ብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መገለጫ ነው ብለዋል። "በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማችን ሴኩላሪዝምን ነው የሚገልፀው፤ ይህም ለአንድ ሃይማኖት ወይም ብሄር ያልወገነና ሁሉንም ህዝቦችና ሃይማኖቶች ፍትሃዊና እኩልነት በሰፈነበት ሁኔታ በገለልተኛነት የሚገለፅ ነው" ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም