የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በገንዘብ የማይተመኑ የማንነት ምልክቶች ናቸው-ዶክተር መንግስቱ ጎበዜ

69
አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2011 የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት በገንዘብ የማይተመኑ የማንነት ምልክቶች በመሆናቸው በአምስት አብያተ ክርስቲያናት ላይ ስጋት የደቀነው መጠለያ በአስቸኳይ እንዲነሳ በቅርሱ ላይ ምርምር የሚያደርጉት ዶክተር መንግስቱ ጎበዜ ተናገሩ። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ ከሚቀጥሉት ሶሰት ዓመታት ወዲህ መጠለያውን ማንሳት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ብሏል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር መንግስቱ ጎበዜ ዓለም አቀፉ የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ 12 ቅርሶችን ሲመዘግብ በዓለም ድንቅ ተብለው ከተመዘገቡት መካከል የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቀዳሚ ናቸው ይላሉ። በ1970ቹ በዓለም አስደናቂ ቅርሶች መዝገብ የሰፈሩ አንጋፋዎቹ የላልይበላ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናት 'ለአካባቢው ማህበረሰብ ማንነቱና እምነቱ ናቸው' የሚሉት ዶክተር መንግስቱ፣ ቅርሶቹ "ለህዝቦች የታሪክ ሽማግሌዎች ትናንትን ለማወቅና ስለነገ ለመተለም ደግሞ ትምህርት ቤት ናቸው" ይላሉ። ዶክተር መንግስቱ ከሰሞኑ በላልይበላ እንደነበሩ ገልጸው፤ የአብያተ ክርስቲያናቱ ለጥገና ተብለው የተወሰዱ መፍትሄዎች ቅርሶችን ለተጨማሪ ስጋት የዳረገና የአካባቢውን ማህበረሰብንም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የጣለ ክስተት መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል። በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ ዘለቀ ከአስር ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የዚህ ዓይነቱን ከወጥ ዓለት የተፈለፈሉ ጥንታዊ ቅርሶቸን መጠገን የሚያስችል ሙያ አልነበረም ይላሉ። በዚህም ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት አደጋ እንዳይደርስባቸው በሚል የ12 ዓመታት ጥናት ተካሂዶ አምስት አብያተ ክርስቲያናቱን ከዝናብና ጸሃይ የሚከለል መጠለያ መሰራቱን ያነሳሉ። ከሶሰት ዓመት ወዲህ ግን ከውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ መካከል ቤተ ገብርኤል ወ ሩፋኤል፣ እንዲሁም አሁን ላይ ቤተ ሚካኤል ጎለጎታ ጥገና እየተደረገላቸው መሆኑን በማንሳት ሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት በሂደት ለመጠገን ልምድና ተሞክሮ እንዳለ ይገልጻሉ። በዚህም ለአምስት ዓመታት ጊዜያዊ መፍትሄ ተብሎ በአምስት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ቤተ ማርያም፣ ቤተ መድሃኒያለም፤ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ ላይ የተሰራው መጠለያ/ሸልተር/ በታቀደለት ጊዜ ሳይነሳ 10 ዓመታት በማስቆጠሩ በቅርሶቹ ላይ ሌላ የአደጋ ስጋት ደቅኗል። ባለስልጣኑ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መጠለያው እንዲነሳ ዩኔስኮን ጨምሮ በመንግስት ይሁንታ ያገኘ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን መጠለያውን ለማንሳት በቅድሚያ አብያተ ክርስቲያናቱን ማደስ ያስፈልጋል ብለዋል። አብያተ ክርስቲያናቱ ሳይታደሱ መጠለያው ቢነሳ ለዓመታት በመጠለያ ስር የነበሩ ቅርሶች በፀሃይና በዝናብ በቀላሉ ለጉዳት ሊጋለጡ ስለሚችሉ በቅድሚያ ቅርሶቹ ካልታደሱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው የሚገልጹት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በባለስልጣኑ ባለሙዎች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መሰረትም ለቅርሶቹ ጥገና ለማድረግ በሚጠይቁ ሶሰት ዓመታት ውስጥ መጠለያው የደቀነው ስጋት 'ጊዜ የሚሰጥ አይደለም' ብለዋል። መጠለያውን ማንሳት የሚያስችል ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ እንዳለ በመጥቀስም፤ በጥናት ሳይደገፍ መጠለያዎቹን በዘመቻ መልክ ማንሳት ለቅርሶቹ ደህንነት ሌላ ችግር እንደሚፈጥር ነው ያነሱት። መጠለያውን በፍጥነት አንስቶ የአብያተ ክርስቲያናቱ ጣራዎች ሳይታደሱ ለሌላ አደጋ ከማጋለጥ ይልቅ መጠለያዎቹን ማጠናከርና ቅርሶቹን እያደሱም ተራ በተራ ማንሳት የተሻለ አማራጭ መሆኑ ታምኖበታል ነው ያሉት አቶ ኃይሉ። ዶክተር መንግስቱ በበኩላቸው ለቅርሶቹ ደህንነት ተብለው የተቀመጡ መጠለያዎች ስጋት  ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በአስቸኳይ መነሳት እንዳለባቸው ይሞግታሉ። 'ጥገናው መቸ ይጀመራል' ለሚለው ጥያቄ አቶ ሃይሉ በሰጡት ምላሽም ባለሰልጣኑ ለቅርሶቹ ጥገናና እድሳት ለማድረግ 3 መቶ ሚሊዮን እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ባለስለጣኑ በዓመት የሚበጀትለት የጥገና ወጭ ከ60 አስከ 70 በመቶውን ወይንም ከ40 ሚሊየን በጀት 20 ሚሊዮኑን ለላልይበላ መመደቡን ገልጸዋል። ነገር ግን የጥገና ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን መጠን ለመሸፈን አቅም አንደሌለው በመግለጽ፤ የላልይበላ ደብርን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ገንዘብ የማሰብሰብ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ነው የሚናገሩት። ዶክተር መንግስቱ በበኩላቸው የላልይበላ አበያተ ክርስቲናት በ300 ሚሊዮን ብር የሚተመኑ ሳይሆኑ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውና ለኢትዮጵያ ማንነት መገለጫዎች በመሆናቸው የገንዘብ ጉዳይ ቅርሶችን ለመታደግ እንደ ምክንያት መቅረብ የሌለበት ጉዳይ ነው ብለዋል። ስለሆነም መንግስት ቅርሶችን ካላቸው ፋይዳና ለቱሪዝም በሚያስገቡት ከፍተኛ ገቢ ግምት ውስጥ በማስገባት አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት አለበት፤ ወይንም ለቤተ ክርስቲያን ኃላፊነቱን በመስጠት በቤተ ክርስቲያን በኩል ተገቢው ጥበቃና እድሳት እንዲደርግላቸው ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም