በሐዋሳ የተከሰተው የእሳት አደጋ የንብረት ውድመት አስከትሏል

57
ሐሙስ ጥቅምት 1/2011 በሀዋሳ ከተማ አሮጌ ገበያ በተከሰተ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ውድመት ማስከተሉን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የተነሳውን የእሳት አደጋ ለመከላከል የከተማው፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የኢንደስትሪ ፓርኩና የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ርብርብ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም በከተማው ውበት ላይ የተሰማሩ የውሃ ማጠጫ ተሽከርካሪዎች እሳቱን ለመቆጣጠር መሰማራታቸው ገልጸዋል፡፡ በገበያው የነበሩት የፍራሽ መጋዘኖችን ጨምሮ ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች ቃጠሎውን እንዳባባሱት ተናግረዋል፡፡ በቃጠሎው ሥፍራ ፈጥነው በደረሱት የሐዋሳ ከተማ እሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች ላይ በተሰነዘረው ጥቃት በተሽከርካሪዎቹና በረዳቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ እንዲሁም የሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች አደጋውን ለመከላከል የያዙትን ውሀ ጨርሰው ለመሙላት ሲንቀሳቀሱ ጉዳት ደርሶባቸው ተመልሰው መሥራት እንዳልቻሉ ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይ የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪን በከተማው መግቢያ ጥቁር ውሀ አካባቢ ጠብቀው መንገድ በመዝጋት ጉዳት ቢያደርሱበትም፤ በፌዴራል ፖሊስና በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ታጅቦ በመግባት እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ የሻሸመኔ ከተማ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪ ቃጠሎው ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይዛመት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ገበያው ሥርዓት ያልያዘና ተቀጣጣይ ነገሮች በአካባቢው ስለነበሩ ለአደጋው ማባባስ  አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡ እሳቱን ለማጥፋት ሲንቀሳቀሱ በነበሩ አካላት ላይ ጉዳት ለማድረስና ሁከት ለመፍጠር ከሞከሩ ግለሰቦች ውስጥ አንዳንዶቹ መያዛቸውን አቶ ስኳሬ አስታውቀዋል። የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር እሳቱን ለመከላከል ላበረከተው አስተዋጽኦ ምክትል ከንቲባው አመሰግነዋል፡፡ የአደጋውን ምክንያትና የንብረት ውድመት ፖሊስ እያጣራ መሆኑም ተገልጿል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም